ኢትዮጵያ በአልሚ ምግቦች፣ በፓስታ እና ማካሮኒ ምርቶች ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ ራሷን ችላለች

147

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 30/2014 (ኢዜአ) ኢትዮጵያ በአልሚ ምግቦች፣ በፓስታ እና ማካሮኒ ምርቶች ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ ራሷን መቻሏን የምግብና መጠጥ ፋርማሲዩቲካል ኢንደስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት ገለጸ።

የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር አቶ ሰለሞን ታደለ የምግብ፣ የመጠጥና የመድሃኒት ፍላጎትን በአገር ውስጥ  ምርቶች ለመተካትና የወጪና ገቢ ንግድ ሚዛኑን ለማጣጣም የተለያዩ ስራዎች እየተሰሩ መሆኑን ገልጸዋል።

ከእነዚህም መካከል እንደ አገር ከውጭ የሚገቡ ፓስታ፣ ማካሮኒ እና አልሚ ምግቦችን በአገር ውስጥ ምርት የመተካት ስራዎችን ጠቅሰዋል።

የፓስታ ምርት በኅብረተሰቡ እየተዘወተረ በመምጣቱ ባለፉት ሁለት ዓመታት የተጠቃሚውን ፍላጎት በአገር ውስጥ ምርት የማሟላት አቅምን ለማሳደግ እየተሰራ እንደሆነ ጠቅሰዋል።

በዚህም በመጀመሪያው ሩብ በጀት ዓመት ፓስታና ለእናቶችና ህጻናት ሰውነት ግንባታ የሚውሉ አልሚ ምግቦችን በአገር ውስጥ የማምረት አቅም 99 በመቶ መድረሱን ገልጸዋል።

የአገር ውስጥ አምራቾች ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎችን መጠቀምና ከውጭ አምራቾች ልምድና ተሞክሮ መውሰዳቸው ለምርት አቅሙ ማደግ አስተዋጽኦ ማበርከቱን ተናግረዋል።

ይህም የውጭ ምንዛሬ ከማዳን በተጨማሪ የአገር ውስጥ ምርቶቹ ተፈጥሯዊ በመሆናቸው ለጤና  ተስማሚነታቸውም የተሻለ መሆኑን አክለዋል።

በእነዚህ ምርቶች የአገር ውስጥ ፍላጎትን ከሟሟላት ባለፈ ለውጭ ገበያ እንዲቀርቡና የምንዛሬ ገቢ እንዲያስገኙ ለማድረግ ጭምር እየተሰራ ነው ብለዋል።

ከተጠቀሱት ምርቶች በተጨማሪም ቢራ አምራቾች የሚጠቀሙበትን የቢራ ብቅል በአገር ውስጥ ምርት የመተካት ስራ በ2014 የመጀመሪያ ሩብ ዓመት 99 ነጥብ 9 በመቶ ማከናወን እንደተቻለ ተናግረዋል።

ይህም የውጭ ምንዛሬ ወጪን ከማዳን በተጨማሪ አምራች አርሶ አደሮችን ተጠቃሚ እያደረገ መሆኑን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም