የውስጥ ባንዳዎችና የውጭ ሃይሎችን ለመመከት የተባበረ ክንድ ያስፈልጋል - ኢዜአ አማርኛ
የውስጥ ባንዳዎችና የውጭ ሃይሎችን ለመመከት የተባበረ ክንድ ያስፈልጋል
ጥቅምት30/2014 የውስጥ ባንዳዎችና የውጭ ሃይሎች በኢትዮጵያ ላይ እያደረሱት ያለውን ጫና ለመመከት የህዝብና መንግስት የተባበረ ክንድ እንደሚያስፈልግ ምሁራን ገለጹ።
የኮተቤ ትምህርት ዩኒቨርሲቲ የታሪክና ህግ ምሑር ዶክተር አልማው ክፍሌ እና የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ድርጅቶች ህብረት ዳይሬክተርና የህግ ባለሙያው መስዑድ ገበየሁ በወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ ከኢዜአ ጋር ቆይታ አድርገዋል፡፡
በቆይታቸውም አሜሪካና አንዳንድ የምእራቡ ዓለም አገራት በሚዲያዎቻቸው ጭምር ኢትዮጵያ ላይ ጫና ለማሳደር የተለያዩ ሙከራዎችን በማድረግ ላይ ይገኛሉ ብለዋል፡፡
በኢትዮጵያ ደካማ፣ ተላላኪ እና በራሱ የማይተማመን መንግሥት እንዲኖር በርካታ ጥረቶችን በማድረግ ላይ መሆናቸውንም ጠቁመዋል።
አሁን ባለው የኢትዮጵያ ሁኔታ የእነርሱን ዕቅድ የሚያሳካ መንግሥት አለመኖሩን ገልጸው፤ ለወደፊትም የማይሳካ ዕቅድ ይዘው በመንቀሳቀስ ላይ መሆናቸውን ዶክተር አልማው ገልጸዋል፡፡
በድርድር ሰበብ አድርገው በኢትዮጵያ አዲስ መንግሥት የመመስረት ዕቅድ እንዳላቸው ማሳየታቸውን ጠቅሰው፤ ፍፁም ተቀባይነት የሌለው መሆኑን ገልጸዋል።
ኢትዮጵያዊያን በራሳቸው ይሁንታ የመረጡት መንግሥት አላቸው ያሉት ዶክተር አልማው፤ በምዕራባዊያን ቡራኬ የሚመጣ ተላላኪ መንግስት ሊኖር አይችልም ብለዋል።
በመሆኑም የውስጥ ባንዳዎችና የውጭ ሃይሎች በኢትዮጵያ ላይ እያደረሱት ያለውን ጫና ለመመከት የህዝብና መንግስት የተባበረ ክንድ ያስፈልጋል ነው ያሉት።
የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ድርጅቶች ህብረት ዳይሬክተርና የህግ ባለሙያው መስዑድ ገበየሁ፤ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ አሜሪካና አንዳንድ የምእራቡ ዓለም አገራት በኢትዮጵያ ላይ ግልጽ ጫና እያሳደሩ ነው ብለዋል።
ኢትዮጵያ ሉዓላዊ አገር በመሆኗ የልማት ግቦቿን ተግባራዊ እንድታደርግ ከቻሉ ማገዝ እንጂ በውስጥ ጉዳይ ጣልቃ መግባት እንደሌለባቸው ገልጸዋል፡፡
የኢትዮጵያ መንግሥት ህዝብ በሰጠው ሉዓላዊ ሥልጣን የህዝቡን ደህንነት ማስጠበቅ የሚችል ጠንካራ መንግሥት መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
ከውስጥም ይሁን ከውጭ በኢትዮጵያ ላይ እየደረሰ ያለውን ጫና ለመቋቋም ሁላችንም በፅናት የምንቆምበት ጊዜ አሁን ነው ብለዋል።