ሩሲያና ቻይና ኢትዮጵያ ላይ የሚደረግ ማዕቀብ የመጣል ሙከራን ተቃወሙ - ኢዜአ አማርኛ
ሩሲያና ቻይና ኢትዮጵያ ላይ የሚደረግ ማዕቀብ የመጣል ሙከራን ተቃወሙ
ጥቅምት 30 ቀን 2014 (ኢዜአ) ሩሲያና ቻይና በኢትዮጵያ ኢኮኖሚያዊ ማዕቀብ ለመጣል የሚደረገውን ሙከራ እንደሚቃወሙ ገለጹ።
የመንግሥታቱ ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት በኢትዮጵያ ወቅታዊ ሁኔታ ዙሪያ ትናንት ማምሻውን በኒውዮርክ ከተማ ተሰብስቦ መክሯል።
በምክክሩ ላይ የተገኙት የሩሲያ እና የቻይና ቋሚ ተወካዮች በኢትዮጵያ ላይ ኢኮኖሚያዊ ጫና ለመፍጠር የሚደረገውን ማንኛውም ሙከራ እንደሚቃወሙ አስታውቀዋል።
ማዕቀብን ጨምሮ ኢትዮጵያ ላይ ኢኮኖሚያዊ ጫና ለመፍጠር የሚደረገው ጥረት የኢትዮጵያን ሕዝብ ፈተና ከማባባስ ባለፈ ግጭቱን ለማስቆም የሚፈይደው አንዳች ነገር አለመኖሩ ነው ሁለቱ አገራት ያስታወቁት።
በተ.መ.ድ የሩሲያ ምክትል ቋሚ መልዕክተኛ አና ኢቪስቲግኔቫ በዚሁ ጊዜ እንዳሉት፤ በተናጠል የሚደረግ ሕገ-ወጥ ማዕቀብ እና የኢኮኖሚ ድጋፍ ክልከላ የከፋ ጉዳት እንዳለው አስምረውበታል።
እንደ እሳቸው ገለፃ፤ የዚህ ዓይነቱ አካሄድ በአገሪቱ ሠላማዊ መፍትሄ ከማስገኘት ይልቅ የዜጎችን እንግልት ያባብሳል።
በኢትዮጵያ ያለውን ችግር ለመፍታት የሚደረገውን አገራዊና ቀጣናዊ ጥረት ከመደገፍ ውጭ ሌላ አማራጭ እንደሌለም አስገንዝበዋል።
የኢትዮጵያ ሉዓላዊነት እና የግዛት አንድነት እንዲጠበቅም ሩሲያ ቁርጠኛ መሆኗን ነው ቋሚ መልዕክተኛዋ ዳግም ያረጋገጡት።
በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የቻይና ቋሚ ተወካይ ጃንግ ጁን በበኩላቸው ቻይና ለአፍሪካውያን ችግሮች ሁሌም አፍሪካዊ መፍትሄዎችን ትደግፋለች ብለዋል።
በኢትዮጵያ ላይ የኢኮኖሚ ዕቀባ አሊያም ድጋፍን ማቋረጥ በፖለቲካዊ እልባት ላይ ጣልቃ መግባት ብቻ ሳይሆን ችግሩን ለመፍታት የሚደረገውን ጥረት የሚጎዳ መሆኑን ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ ህዝብ አሁን የገጠመውን ፈተና በድል ለመወጣት፣ አገራዊ አንድነትን ለማስጠበቅ እና በአገሪቷ ሠላምና መረጋጋት ለመፍጠር እንዲሁም የልማትና የመነቃቃት ጉዞውን ለማስቀጠል የሚያስችል አቅምና ጥበብ እንዳለው እምነታቸውን ገልጸዋል።
እየታየ ያለውን የኢትዮጵያን ህዝብ ጥረት ለማስቀጠልም ከዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ጋር ለመስራት ቻይና ዝግጁ መሆኗን ጃንግ ጁን አረጋግጠዋል።
_ አካባቢህን ጠብቅ፣
_ ወደ ግንባር ዝመት፣
_ መከላከያን ደግፍ።