በተግባር ላይ ያለው የትምህርት ፖሊሲ ውጤታማ ባለመሆኑ በርካታ ችግሮች ታይተዋል--ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐብይ - ኢዜአ አማርኛ
በተግባር ላይ ያለው የትምህርት ፖሊሲ ውጤታማ ባለመሆኑ በርካታ ችግሮች ታይተዋል--ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐብይ
አዲስ አበባ ነሀሴ 14/2010 በኢትዮጵያ በተግባር ላይ ያለው የትምህርት ፖሊሲ የታሰበውን ያህል ውጤታማ ባለመሆኑ አገሪቱ ችግሮች ሲገጥሟት መቆየቱን ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ገለጹ። የትምህርትና ስልጠና ፍኖተ-ካርታ ዛሬ በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ውይይት እየተደረገበት ነው። ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ በውይይቱ ላይ እንደገለጹት ላለፉት 20 ዓመታት በተግባር ላይ ያለው የትምህርት ፖሊሲ ያስገኘው ጥቅም እንዳለ ሆኖ በአብዛኛው ፍሬያማ አልነበረም። ኢትዮጵያ የውሃ ሀብት፣ ለም መሬትና አምራች ዜጋ ያላት ብትሆንም አገሪቱ መለወጥና መልማት እንዳልቻለች ገልጸዋል። ችግሩ በዚህ ብቻ የሚያበቃ እንዳልሆነ የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ በአሁኑ ወቅት በሕክምና፣ በግንባታ፣ በፍትህና በፋይናንስ ተቋማት ላይ በኃላፊነት የማይሰሩ ዜጎች ተበራክተው ይገኛሉ ብለዋል። እንደ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገለጻ የትምህርት ፖሊሲው ለአገር በቀል እውቀቶች ትኩረት ያልሰጠና ለምዕራባውያን ፍልስፍና ያጋደለ በመሆኑ ብቁ ዜጋ ማፍራት አልተቻለም። በተጨማሪም ለብዛት እንጂ ለጥራት ትኩረት ያልሰጠ ከመሆኑም ባሻገር ለማሻሻል ዕድል የማይሰጥ ስለሆነ ብቃት የሌላቸው ዜጎች እንዲወጡ ምክንያት ሆኗል። ችግሩ ሁሉን አቀፍ መሆኑን የጠቀሱት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ፖሊሲው ከሥርዓተ ትምህርት ዝግጅት፣ ከመምህራን ስልጠና፣ ቴክኖሎጂን አለመጠቀምና መዋቅራዊ ችግር ያለበት በመሆኑ ከፍተኛ የፍትሃዊነት ጥያቄ የሚያስነሳ ነው ብለዋል። 'የኢትዮጵያ ትምህርት ከየት ወዴት' በሚል ጽሑፍ ያቀረቡት የትምህርት ሚኒስትሩ ዶክተር ጥላዬ ጌቴ በትምህርትና ስልጠና ዘርፍ ያለው ችግር እጅግ ስር የሰደደ በመሆኑ አዲስ ፍኖተ-ካርታ ማዘጋጀት አስፈልጓል ብለዋል። ከችግሮቹ መካከል ለቅድመ መደበኛ ትምህርት የተሰጠው ትኩረት አነስተኛ መሆን፣ ኢ-ፍትሃዊነት፣ በሁለተኛ ደረጃ ትምህርት በክልሎች መካከል ያለው የአፈጻጸም ልዩነትና አዝጋሚ እድገት ተጠቃሽ መሆናቸውን ተናግረዋል። እንዲሁም የትምህርት ተቋማት አደረጃጀት ብቃት ማነስ፣ ከዘመኑ ጋር አብሮ በማይራመድ ስርዓተ ትምህርት መመራት፣ የመምህራን መልመላና ዝግጅት ችግር እንዲሁም የተማሪዎች ውጤት ማሽቆልቆል አሳሳቢ እንደሆነም ገልጸዋል። እንደ ዶክተር ጥላዬ ማብራሪያ የትምህርትና ስልጠና ፖሊሲው ከቅድመ መደበኛ እስከ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ድረስ እጅግ ውስብስብና መፍትሄ የሚፈልግ በመሆኑ ፍኖተ-ካርታውን ተግባራዊ ማድረግ አስፈላጊ ነው። ፍኖተ-ካርታውን ካዘጋጁት መካከል የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ፕሮፌሰር ጣሰው ወልደሃና በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ላይ ባቀረቡት ጽሑፍ እንደገለጹት በትምህርት ተቋማቱ ላይ የሚታየው ችግር አሳሳቢ ደረጃ ላይ ደርሷል። በአሁኑ ወቅት ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት እየተመረቁ የሚወጡ ተማሪዎች 80 በመቶ የሚሆኑት የሌላ ሰው ጥናት ገልብጠው የራሳቸው አስመስለው የሚያቀርቡ ናቸው ብለዋል። በተጨማሪም አንዳንድ ዩኒቨርሲቲዎች ላብራቶሪ እንኳን ሳይኖራቸው ለአምስት ዓመታት በኢንጂነሪንግ ዘርፍ ተማሪዎችን አስመርቀዋል ያሉት ፕሮፌሰር ጣሰው በስርዓተ ትምህርት ቀረጻ ረገድ ግለሰቦችን ታሳቢ አድርገው የተጀመሩ መርሃ-ግብሮች አሉ ብለዋል።
ፕሮፌሰር ጣሰው እንዳሉት የጥራት ችግሮችን ለመፍታት የከፍተኛ ትምህርት ተቋማትን አግባብነትና ጥራት የሚከታተል ገለልተኛ ተቋም ባለመኖሩ ችግሩ እንዲባባስ ሆኗል። ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን በበኩላቸው በሥራ ላይ ያለው የትምህርት ፖሊሲ ያሉበት ችግሮች በአግባቡ ባለመተግበሩ ይበልጥ ተባብሰዋል ነው ያሉት። የፍኖተ-ካርታው ፍልስፍና የሚሻሽልና የአገሪቱን የዕድገት ደረጃ የሚመጥን መሆኑን ጠቅሰው በትምህርት ስርዓቱ ላይ የሚታዩትን ችግሮች የለየና የመፍትሄ አቅጣጫም ያስቀመጠ ነው ብለዋል። በመሆኑም ችግሮችን ለመፍታት ሁሉም ባለድርሻ አካላት በፍኖተ-ካርታው ላይ ዝርዝር ውይይት እንዲያደርጉ አሳስበዋል። ከ26 ዘርፎች የተወጣጡ 1 ሺህ 300 ባለድርሻ አካላት በውይይቱ የተገኙ ሲሆን በቅድመ መደበኛ እና በመደበኛ፣ በቴክኒክና ሙያ ስልጠና፣ በከፍተኛ ትምህርት፣ በመምህራን ምልመላ እና በአጠቃላይ ትምህርት መዋቅር ዙሪያ ያሉ ችግሮች ቀርበዋል። ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች በተገኙበት በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት በመካሄድ ላይ ያለው ውይይት ለሦስት ቀናት ይቀጥላል።