የምዕራብ ጎንደር ነዋሪዎች ዝመት፣መክትና ደግፍን በተግባር እያረጋገጡ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የምዕራብ ጎንደር ነዋሪዎች ዝመት፣መክትና ደግፍን በተግባር እያረጋገጡ ነው
መተማ፣ ጥቅምት 30/2014 (ኢዜአ)የምዕራብ ጎንደር ዞን የሁለት ከተሞች ነዋሪዎች ዝመት፣መክትና ደግፍን በተግባር እያረጋገጡ ነው።
በምዕራብ ጎንደር ዞን የገንዳ ውሃና የመተማ ዮሐንስ ከተሞች ነዋሪዎች ኢትዮጵያ ሕልውናዋን ለማስከበር ያቀረበቻቸውን ሦስቱን ጥያቄዎች እየመለሱ ነው።
ነዋሪዎቹ ከሀገር መከላከያ ሠራዊትና ከፀጥታ ኃይሎች ጋር በመሆን አሸባሪው ህወሓትን በኢትዮጵያዊ የጀግንነት ወኔ እየተዋጉ፣ በዘማችነት እየተሳተፉና የሕልውና ዘመቻውን በገንዘብና በቁሳቁስ እየደገፉ ይገኛሉ።
አሸባሪው ህወሓት በንጹሃን ዜጎች ላይ ኢ-ሰብዓዊ ድርጊቶችን በመፈጸም ሀገር የማፍረስ እኩይ ተልዕኮውን ለማሳካት እያደረገ ያለውን መንፈራገጥ ገተው መውጫ ቀዳዳ እያሳጡት ነው።
የሀገር መከላከያ ሠራዊትን ማጠናከርንም የሕልውናው ዘመቻ አካል አድርገው እየተገበሩት ይገኛሉ።
የከተሞቹ ነዋሪዎች ለኢዜአ በሰጡት አስተያየት ወራሪውና ተስፋፊውን የህወሓት አሸባሪ ቡድን በመመከት ሕልውናቸውን እያስጠበቁ መሆናቸውን ተናግረዋል።
ከገንዳ ውሃ ከተማ ነዋሪዎች መካከል አቶ ይመር ዓሊ እንዳሉት ''ዳግም የባርነትን ቀንበር መሸከም የሚችል ትከሻ የለንም።''
''በሕዝባዊ አደረጃጀት ታቅፌ አካባቢዬን በንቃት እየጠበቅኩ ነው'' ሲሉም ከህብረተሰቡ ጋር በመሆን የአሸባሪውን ህወሓት ቅጥረኞችና ሰርጎ ገቦችን እየተከላከሉ መሆናቸውን ተናግረዋል።
አቶ ይመር ጠላትን ግንባር ሄደው በመመከትና በመደምሰስ ተሳትፎ ማድረጋቸውን አስታውቀዋል።
ለሕልውና ዘመቻው እስካሁን 5ሺህ ብርና ግማሽ ኩንታል ዱቄት ድጋፍ ማድረጋቸውን ገልጸው፤ድጋፋቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ አረጋግጠዋል።
የመተማ ዮሐንስ ከተማ ነዋሪ አቶ አስማማው በለጠ ከዚህ በፊት በተለያዩ ግንባሮች ዘምተው ጠላትን መዋጋታቸውን ገልጸዋል።
ለሕልውና ዘመቻው 3ሺህ ብር በጥሬ ገንዘብ እና ከ6 ሺህ ብር በላይ የሚገመት የአይነት ድጋፍ ማድረጋቸውንም ተናግረዋል።
ከተማዋ ከጎረቤት ሀገር ጋር የምትዋሰን እንደመሆኗ ጥበቃውን በማጠናከርና ጠላት ገፍቶ ከመጣም ለመደምሰስ አስፈላጊውን ዝግጅት ማድረጋቸውን አስታውቀዋል።
ሌላው አስተያየት ሰጪ አቶ መኳንንት ባይተኩስ በበኩላቸው አገርን እንደ አገር፣ አማራን እንደ ሕዝብ ለመታደግ አካበቢያቸውን እየጠበቁ መሆናቸውን ተናግረዋል።
''አሁን ጊዜው ጠላትን ቀን ከሌሊት የንስር ዓይን ሆኖ መጠበቅና በየትኛም ጊዜና ቦታ ሲገኝ 'አይቀጡ ቅጣት' የሚቀጣበት ነው'' ብለዋል።
''የኢትዮጵያ አሸናፊነት ጥርጥር የሌለው ቢሆንም ጊዜ በረዘመ ቁጥር ሕዝቡ በደል እየደረሰበት ነው''ያሉት አቶ መኳንንት፣ የኢትዮጵያ ሕዝብ የሽብርተኛው ቡድን ግብዓተ መሬት ለማፋጠን እንዲረባረብ ጠይቀዋል።
ህብረተሰቡ ''ቅድሚያ ለአገሬ'' በማለት ከዕለት ጉርሱ እየቀነሰ ለጀግናው የሀገር መከላከያ ሠራዊት፣ ለአማራ ልዩ ኃይል፣ ለሚሊሻና ለፋኖ ስንቅ በማዘጋጀት ላይ ነው ያሉት ደግሞ የገንዳ ውሃ ከተማ ነዋሪዋ ወይዘሮ ትዕግሥት መላኩ ናቸው።
አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ ወደ ግንባር እንደሚሄዱ የገለጹት አስተያየት ሰጪዋ፣ ፀጉረ ልውጦችን በመከታተል ለፀጥታ አካሉ ደጀንነታቸውን በተግባር እንደሚያረጋግጡም ተናግረዋል።