የኢትዮጵያን ሉአላዊነት ለማስከበር በሚደረገው የህልውና ዘመቻ ለመሰለፍ ተዘጋጅተናል - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያን ሉአላዊነት ለማስከበር በሚደረገው የህልውና ዘመቻ ለመሰለፍ ተዘጋጅተናል
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 30/2014 (ኢዜአ) ''መንግስት የረጅም ጊዜ ጥያቄያችንን ስለተቀበለን የኢትዮጵያን ሉአላዊነት ለማስከበር በሚደረገው የህልውና ዘመቻ በቁርጠኝነት ለመሰለፍ ተዘጋጅተናል ሲሉ የቀድሞ የኢትዮጵያ ጦር ሰራዊት አባላት ገለጹ።
የአገር መከላከያ ሚኒስቴር ባለፈው ሳምንት የቀድሞ የሰራዊት አባላት በሚችሉት አቅም የህልውና ትግሉን እንዲያግዙ ጥሪ ማቅረቡ ይታወቃል።
ይህንንም ተከትሎ የቀድሞ የኢትዮጵያ ሰራዊት የድጋፍና ልማት ማሕበር መንግስት ለቀድሞ የሰራዊት አባላት ያደረገውን ጥሪ አስመልክቶ መግለጫ ሰጥቷል።
የማሕበሩ ፕሬዚዳንት ሃምሳ አለቃ ብርሃኑ አማረ፤ በሰጡት መግለጫ መንግስት ያደረገው ጥሪ የቀድሞ ጦር ሰራዊት አባላትን ያስደሰተ መሆኑን ገልጸዋል።
ከማንኛውም ጉዳይ በላይ የአገርን ሉአላዊነት ለማስጠበቅ የተዋደቁ የቁርጥ ቀን ልጆች መሆናቸውን ጠቅሰው መንግስት ለህልውና ትግሉ እንዲሰለፉ እድል እንዲያመቻችላቸው ጠይቀው እንደነበረ አንስተዋል።
ኢትዮጵያ በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ በመሆኗ መንግስት ላደረገው ጥሪ አገራዊ ምላሽ ለመስጠት መዘጋጀታቸውን ገልጸው ማህበሩ በሁሉም የአገሪቷ አካባቢዎች የሚገኙ የቀድሞ ሰራዊት አባላትን ያስተባብራል ብለዋል።
የቀድሞ የሰራዊት አባላት በቀጥታ በግንባር መሰለፍ፣ ልምድና እውቀታቸውን በማጋራት እንዲሁም በማሰልጠን ጉልህ ሚና እንደሚኖራቸው ሃምሳ አለቃ ብርሃኑ ገልጸዋል።
የቀድሞ የሰራዊት አባላቱ በመንግስት የመጣውን ጥሪ በመቀበል ለአገራቸው በድጋሚ ታሪካዊ ሃላፊነታቸውን እንዲወጡ ጠይቀዋል።
በጥሪው መሰረት በእድሜ ጣራ ላይ የተቀመጠው ገደብ የተወሰኑ የሰራዊት አባላት ተሳትፎ ሊገታ ይችላል ያሉት ሃምሳ አለቃ ብርሃኑ ማሕበሩ ከመንግስት ጋር በቅርበት ለመነጋገር አስቧል ብለዋል።