ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ የቁርጥ ቀን ልጆች አሸባሪውን በመቅበር ታሪክ የማይሽረው ገድል እየፈፀሙ ነው

 ጥቅምት 30/2014(ኢዜአ) የኢትዮጵያ የቁርጥ ቀን ልጆች አሸባሪውን በመቅበር ታሪክ የማይሽረው ገድል እየፈፀሙ መሆኑን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ ተናገሩ።

ከንቲባዋ በወሎ ግንባር ተገኝተው የህወሓትን የሽብር ቡድን እየተፋለመ ለሚገኘው የጸጥታ ኃይል 20 ሚሊዮን ብር የሚገመቱ ሰንጋዎችና የተለያየ የቁሳቁስ ድጋፍ አበርክተዋል።

 የመከላከያ ሠራዊቱ ለአገር ሉዓላዊነትና ክብር በምንም የማይከፈል ታላቅ ተጋድሎ እየፈጸመ መሆኑን ተናግረዋል።

 የኢትዮጵያ የቁርጥ ቀን ልጆች አገር ከሌለ መኖር ትርጉም የለውም በሚል ወኔ ታሪክ የማይሽረው ገድል እየፈጸሙ መሆኑን ገልጸዋል።

 የጸጥታ ኃይሉ በሽብር ቡድኑ ላይ እየወሰደ ያለው እርምጃና እየፈጸመ የሚገኘው ጀብዱ ለዛሬ ብቻ ሳይሆን ለቀጣዩ ትውልድም ማስተማሪያ የሚሆን ነው ብለዋል። 

አሸባሪው ህወሃትንና የእርሱን ተላላኪዎች በመቅበር ኢትዮጵያን ወደ ከፍታ እናወጣታለን ሲሉም ነው የተናገሩት፡፡

የኢትዮጵያ ሕዝብም ከጸጥታ ኃይሉ ጎን በመቆም 'ኢትዮጵያን እናፈርሳለን' የሚሉትን ለማፍረስ እስከ ሕይወት መስዋዕትነት ለመክፈል መዘጋጀቱንም ነው የገለጹት። 

በመሆኑም ሠራዊቱ ሙሉ ትኩረቱን የሽብር ቡድኑ ላይ አድርጎ በአጭር ጊዜ መደምሰስ እንዲችል ለሠራዊቱ አባላት ቤተሰቦችም አስፈላጊውን ድጋፍ እናደርጋለን ብለዋል። 

ሰራዊቱንና የሰራዊቱን ቤተሰቦች መደገፍ የአመራሩ ብቻ ሳይሆን የሁሉም ኢትዮጵያውያን ኃላፊነት መሆኑንም አንስተዋል፡፡ 

ድጋፉን የተቀበሉት የመከላከያ ሠራዊት ተወካይ ሜጀር ጄኔራል ሀብታሙ ጥላሁን የሠራዊቱ የጥንካሬና የአሸናፊነት ምንጭ የኢትዮጵያ ሕዝብ ደጀንነት ነው ብለዋል። 

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ያደረገልን ድጋፍም ተጨማሪ ሞራልና መነሳሳት ይፈጥራል ነው ያሉት። 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም