ቀጥታ፡

ለቀድሞ ሰራዊት ጥሪ መደረጉ ለወታደራዊ ግዳጅ አፈጻጸም ውጤታማነት ወሳኝ ነው

ጥቅምት 30/2014(ኢዜአ)  ለቀድሞ የኢትዮጵያ ሰራዊት ጥሪ መደረጉ ለወታደራዊ ለግዳጅ አፈጻጸም ውጤታማነት ወሳኝ እንደሚሆን የቀድሞ ከፍተኛ የጦር መኮንኖች ተናገሩ።

ኢትዮጵያ በታሪኳ በየትኛውም ከሃዲና ወራሪ ጠላት ተደፍራ አታውቅም አሁንም የሁን ወደ ፊት አናስደፍራትም ብለዋል።
ብርጋዴር ጀኔራል ሰብስቤ ንጋቱ እና ኮሎኔል ገበየሁ አበበ፤ በስመ ጥሩ የቀድሞው ገነት ጦር ትምህርት ቤት በማመር በ1953 ዓ.ም የተመረቁ በቀድሞ ጦር ሰራዊት የአየር ወለድ ኮማንዶ መኮንኖች ናቸው።

ሁለቱም መኮንኖች ወደ አሜሪካና ሩስያ በማቅናትም የተለያዩ ወታደራዊ ትምህርቶችን ወስደው በመመለስ አገራቸውን አገልግለዋል።

ብርጋዴር ጀኔራል ሰብስቤ በ4ኛ ክፍለ ጦር እና በታጠቅ ክፍለ ጦር በአሰልጣኝነት፣ በምስራቅ ኢትዮጵያ የ11ኛ ብርጌድ ዘመቻ መኮንንነት፣ በላይዘን ኦፊሰርነት፣ በአየር መንገድ በረራ ደህንነት በድምሩ ከ31 ዓመታት በላይ አገልግለዋል።

በሰሜን ኢትዮጵያ አስቸጋሪውን የናቅፋ ውጊያ ጨምሮ በተለያየዩ ጦር ክፍሎች የኢትዮጵያን የግዛት አንድነት የማስጠበቅ ዘመቻዎች በአዋጊነት የመሩ ሲሆን ከመንግስት ለውጥ በኋላ በወያኔ ስርዓት ለ7 ዓመታት በግፍ ታስረዋል።

ከብርጋዴር ጀኔራል ሰብስቤ ጋር አንድ ኮርስ የነበሩት ኮሎኔል ገበየሁ አበበ፤ ከገነት ጦር ትምህርት ቤት በመኮንነት ከተመረቁ በኋላ በ4ኛ አየር ወለድ ፓራኮማንዶ አሰልጣኝነት፣ በወታደራዊ ፖሊስነትና በበረራ ደህንነት አገራቸውን አገልግለዋል።

ከጀግናው አሊ በርኬ ጋር በምስራቅ ኢትዮጵያ ከሶማሊያ ጋር በተደረጉ ውጊያዎች እንዲሁም ወደ ሰሜን ኢትዮጵያ ጦር ግንባር በ30ኛ ሻለቃ፣ በ6ኛ፣ በ8ኛ፣ በ10ኛና በ46ኛ ብርጌዶች እንዲሁም የ21ኛ ክፍለ ጦር አዛዥነት በአጠቃላይ ለ17 ዓመታት በሰሜን ኢትዮጵያ ቆይተዋል።

ከኢዜአ ጋር ቆይታ ያደረጉት ሁለቱ የጦር ሜዳ ጀግኖች የአሸባሪውን ህወሃት አይነተኛ መገለጫዎች ያብራራሉ።

አሸባው ሃይል በባንዳነት አገራቸውን የሚክዱ፣ ሰላማዊ ሰዎችን በመግደል የተካኑ፣ በተንኮልና ሴራ የተጠመዱ፣ ስርቆትና ዝርፊያም ከባህሪዎቻቸው መገለጫዎች መካከል መሆናቸውን ጠቅሰዋል።

ለአሸባሪው ቡድን አረመኔነት መገለጫ ለዘመናት አብረው የኖሩና የተዛመዱ የሰራዊት አባላትን ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም በሌሊት ከመጨፍጨፍ በላይ የጭካኔ ጥግ የለም ይላሉ መኮንኖቹ።

አሸባሪው ቡድን ስልጣን ወይም ሞት፤ ካልሆነም ኢትዮጵያ ትፍረስ ብሎ የተነሳ ባንዳ መሆኑን ተናግረው እቅዱን ለማሳካት ከውስጥም ከውጭም ሃይሎች ጋር እየሰራ መሆኑን አብራርተዋል።

የውጭ ሃይላት ኢትዮጵያን በወያኔ በኩል በመከፋፈል ለመነጣጠል ቢሞክሩም ዛሬም አገር ሲወረር ወጣቱ ለአገሩ ህልውና ሲል እየተመመ በመሆኑ አድንቀዋል።

ኢትዮጵያ ዛሬ ሳይሆን ትናንትም በአድዋም ሆነ በሁለተኛው የፋሺስት ወረራ ባላት ባህላዊ መሳሪያ ቅኝ ግዛትን በማክሸፍ በአፍሪካ የነጻነት ፋና ወጊ መሆኗን ታሪክ አይዘነጋውም።

ለዚህ ደግሞ የኢትዮጵያ የቁርጥ ቀን ልጆች በጀግንነት የአገራቸውን ክብርና ነፃነት አስከብረው መዝለቃቸውን መኮንኖቹ ገልጸዋል።

የቀድሞ የአገር መከላከያ ሰራዊት ለአገራቸው ሉአላዊነት የከፈሉትን መስዋእትነትና አሁንም ያላቸውን ቁርጠኝነት በመግለጽ አሁንም ለአገር ህልውና ዘመቻው መጠራታቸው ተገቢ ነው ሲሉ አድንቀዋል።

በመንግስ ጥሪ እንዲደረግና ከማማከር እስከ ቀጥታ የግንባር ውጊያ እንዲሰለፍ ጥያቄ ሲያቅርብ እንደነበር አስታውሰው አሁን ላይ ምላሽ መሰጠቱ ተገቢ ነው ብለዋል።

የቀድሞ ጦር ሰራዊት የካበተ ልምድ ስላላቸው በተለያዩ የሙያ መስኮች ስምሪት ተሰጥቷቸው ለአገራቸው ህልውና ጉልህ ሚና ይኖራቸዋል የሚል እምነት እንዳላቸው ገልጸዋለ።

የኢትዮጵያ ታሪክ የአሸናፊነት እንጂ በየትኛውም ከሃዲና ወራሪ ጠላት ተደፍራ አታውቅም፤ አሁንም ወደ ፊትም አናስደፍራትም ብለዋል ከፍተኛ የጦር መኮንኖቹ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም