ቀጥታ፡

በኢትዮጵያ የተከሰተውን ችግር ለመፍታት ሉዑላዊነትን ባከበረ መልኩ በገለልተኛነት መንቀሳቀስ ይገባል

ጥቅምት 30 ቀን 2014 (ኢዜአ) በውስጥ ጉዳይ ጣልቃ ባለመግባት፣ ፖለቲካዊ ገለልተኝነትን በማሳየትና ሉዑላዊነት በማክበር ኢትዮጵያ ውስጥ የተከሰቱ ችግሮችን ለመፍታት መንቀሳቀስ እንደሚገባ የአፍሪካ ህብረት አስታወቀ።

የአፍሪካ ሕብረት የጸጥታው ምክር ቤት በኢትዮጵያ ወቅታዊ ጉዳይ ላይ ከመከረ በኋላ የአቋም መግለጫ አውጥቷል።

በመግለጫውም “በኢትዮጵያ የተከሰቱ ችግሮችን ለመፍታት የሀገሪቱን ሉዐላዊነት ባከበረ መልኩ ከባለድርሻ አካላት ጋር መስራት እንደሚገባ በድጋሚ አረጋግጣለሁ” ብሏል።

ሕብረቱ ከመንግስትና ከሌሎች አካላት ጋር የተፈጠሩ ችግሮችን ለመፍታት በሚያከናውናቸው ተግባራት ፖለቲካዊ ገለልተኛነቱን ጠብቆ እንደሚጓዝ አስታውቋል።

በተጨማሪም የኢትዮጵያን የውስጥ ጉዳይ ለህዝቦቿ በመተው በአጋርነት መንፈስ እንደሚሰራ አረጋግጧል።

በሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍልና አሸባሪው ህወሃት በወራረቸው የአፋርና የአማራ ክልሎች ያለው የጸጥታ ሁኔታ እንደሚያሳስበው ያመለከተው ህብረቱ፤ በኢትዮጵያ ሰላም ማረጋገጥ ለቀጣናውም ሆነ ለአፍሪካ ወሳኝ መሆኑን አስታውቋል።

ኢ-ህገመንግስታዊ በሆነ መንገድ መንግስትን ለመቀየር የሚካሄዱ ተግባራትን እንደሚቃወም ገልጾ፤ ድርጊቱ በአህጉሩ የዴሞክራሲና መልካም አስተዳደር ባህልን ለማሳደግ የሚካሄደውን እንቅስቀሴ የሚጻረር መሆኑን አመላክቷል።

አንዳንድ አለም አቀፍ ተቋማትና ምእራባውያን አለም አቀፍ ህጎችን በመጻረር የሚያደርጉትን ለአንድ ወገን ያደላ አካሄድም እንዲያስተካክሉ ጠይቋል።

ግጭቶች በተከሰቱባቸው አካባቢዎች የሚገኙ ሁሉም አካላት የተኩስ አቁም እንዲያደርጉም ነው የጠየቀው።

በኢትዮጵያ የዴሞክራሲያዊና የመልካም አስተዳደር ፍሬዎች እንዲታዩ ሁሉን ያማከለ ብሔራዊ ውይይቶችን ማካሄድ እንደሚገባ አመልክቶ ሕብረቱም በዚህ ረገድ ከኢትዮጵያ ጎን ሆኖ እንደሚንቀሳቀስ ገልጿል።

በተለይም ህብረቱ የወከላቸው የቀድሞው የናይጄሪያ ፕሬዚዳንት ኦሊሴጉን ኦባሳንጆ የሚያደረጉትን እንቅስቃሴ በብርቱ እንደሚደግፍና የአፍሪካውያንን ችግር አፍሪካዊ መፍትሄ ለመስጠት ኢትዮጵያውያንም ድጋፋቸውን እንዲሰጡ ጠይቋል።

በተፈጠረው ችግር የተነሳ የተከሰቱ የሰብአዊ መብት ጥሰቶችንና ከፍተኛ ወንጀሎችን ለማጣራትና ይህን ያደረጉ አካላትን ተጠያቂ ለማድረግ ሁሉም የድርሻውን እንዲወጣ አሳስቧል።

በብሔር፣ በጾታ፣ በሐይማኖትና  በቋንቋ ምክንያት የሚደርሱ ጥቃቶች እንዲቆሙ ርብርብ እንዲደረግ ለፖለቲካ ፓርቲዎችና ለባለድርሻ አካላት ጥሪውን አስተላልፏል።

መገናኛ ብዙሃንም ሙያዊ ሃላፊነት በተሞለበት መልኩ ስራቸውን በአግባቡ ማከናወን እንደሚገባቸው ነው የአፍረካ ህብረት ያሳሰበው።

_ አካባቢህን ጠብቅ፣

_ ወደ ግንባር ዝመት፣

_ መከላከያን ደግፍ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም