በኤሌክትሪክ መሰረተ ልማቶች ላይ ከ4 ሚሊዮን ብር በላይ ግምት ያለው ንብረት ስርቆት ተፈጽሟል - ኢዜአ አማርኛ
በኤሌክትሪክ መሰረተ ልማቶች ላይ ከ4 ሚሊዮን ብር በላይ ግምት ያለው ንብረት ስርቆት ተፈጽሟል
ሃዋሳ ጥቅምት 30/2014 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ባለፉት ሦስት ወራት ከ4 ሚሊዮን ብር በላይ ግምት ያላቸው የኤሌትሪክ መሰረተ ልማቶች ላይ ስርቆት መፈጸሙን አስታወቀ።
በኤሌክትሪክ መሰረተ ልማቶች ላይ ከጊዜ ወደጊዜ እየተባባሰ የመጣውን የስርቆት ወንጀል ለማስቀረት የሚመለከተው አካል ትኩረት እንዲሰጥም ተጠይቋል።
በአገልግሎቱ የደቡብ ሪጂን የህግ አገልግሎት ሃላፊ አቶ አብዲ ስንታቸው እንደገለጹት በሪጂኑ ባለፉት ሦስት ወራት ብቻ ከ4 ነጥብ 1 ሚሊዮን ብር በላይ በሚያወጡ የኤሌክትሪክ መሰረተ ልማቶች ላይ ስርቆት ተፈጽሟል።
የኤሌክትሪክ ሃይል አስተላላፊ ሽቦና ተሸካሚ ምሰሶዎች በዋናነት በከፍተኛ ሁኔታ ስርቆት የሚፈጸምባቸው መሆናቸውንም ተናግረዋል።
"በተለይ በደቡብ ክልል በወላይታ፣ ካምባታና ጣምባሮ ዞኖች እንዲሁም በሲዳማ ክልል አንዳንድ አካባቢዎች የኤሌክትሪክ መሰረተ ልማት ስርቆት ከጊዜ ወደጊዜ እየተስፋፋ መጥቷል" ብለዋል።
ለአብነትም ከቢሻን ጉራቻ እስከ ሃዋሳ አየር ማረፊያ ድረስ የሚዘልቅ ከ20 ኪሎ ሜትር በላይ የተዘረጋ የኤሌክትሪክ ሃይል ተሸካሚ መስመር ተሰርቆ በአሁኑ ወቅት አገልግሎት መቋረጡን ተናግረዋል።
እንደ ሀላፊው ገለጻ ወንጀሉን ፈጽመዋል በሚል የተጠረጠሩ ከ40 በላይ ግለሰቦች ጉዳያቸው በህግ ሂደት ላይ ይገኛል።
ህብረተሰቡ አጥፊዎችን አጋልጦ በመስጠትና ወንጀለኞችም ተገቢውን ፍርድ እንዲያገኙ ከማድረግ አንጻር የሚስተዋለውን ከፍተት ለማረም ልዩ ትኩረት እንደሚሻም ተናግረዋል።
በመሰረተ ልማቶች ላይ የሚደርሰው ጉዳት የማህበረሰቡን የኤለክትሪክ ሀይል ፍላጎት ከመግታት ባሻገር በሃገር ሀብትና ልማት ላይ እያደረሰ ያለው ጉዳት ከፍተኛ መሆኑንም አስረድተዋል።
በመሆኑም የሚመለከታቸው የህግ አካላት ትኩረት እንድሰጡት ጠይቀዋል።
በጉምሩክ ኮሚሽን ሃዋሳ ቅርንጫፍ ሻሸማኔ መቆጣጠሪያ ጣቢያ ምክትል ሃላፊ ኢንስፔክተር ተክሌ አጥሮ በበኩላቸው፣ ባለፈው በመስከረም 2014 ዓ.ም 28 ከፍተኛ የኤሌክትሪክ ሃይል አስተላላፊ ጥቅል ሽቦ መያዙን ገልጸዋል።
ንብረቱ የተያዘው የሰሌዳ ቁጥር ኮድ 3A-60893 አአ በሆነ አይሱዙ ተሽከርካሪ አሮጌ ብረታ ብረት የጫነ ቁሳቁስ በማስመሰል ለማሳለፍ ሲሞከር ከህብረተሰቡ በደረሰ ጥቆማ መሰረት መሆኑን ተናግረዋል።
ከወንጀሉ ጋር በተያያዘ አሽከርካሪው፣ ረዳቱና ተሽከርካሪው በቁጥጥር በሕግ ቀጥጥር ስር እንዲውሉ መደረጋቸው ገልጸዋል።
የተያዘው የኤሌክትሪክ እቃ ግምት ከ1 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር በላይ መሆኑንም ኢንስፔክር ተክሌ ተናግረዋል።
በአሁኑ ወቅት በኤሌክትሪክ መሰረተ ልማቶች ላይ እየደረሰ ያለውን ውድመት ለመከላከል ማህበረሰቡ የጀመረውን ተሳትፎ አጠናክሮ እንዲቀጥልም አሳስበዋል።።