ቀጥታ፡

ፌዴራል ፖሊስ የደንብ ልብስና ዓርማ ቀየረ

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 29 ቀን 2014 (ኢዜአ) የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን ሲጠቀምበት የቆየውን የደንብ ልብስና ዓርማ መቀየሩን ይፋ አድርጓል።

የደንብ ልብሱ የተቀየረው ተመሳስለው በተሰሩ የደንብ ልብሶች ወንጀሎች እንዳይሰሩ ለመከላከል መሆኑን ኮሚሽኑ አዲሱን የደንብ ልብስ ባስተዋወቀበት መርሃ ግብር ላይ አስታውቋል።

በዚሁ መሰረት እግረኛ፣ ኮማንዶና በተለያዩ ደረጃዎች የሚገኙ የፌዴራል ፖሊስ አባላት የደንብ ልብስ ተቀይሯል።

የደንብ ልብሱ ከቀድሞው በተለየ መልኩ የኢትዮጵያ ባንዲራ በቀኝ እጅና በደረት ላይ ተቀምጦበታል።  

በኮሚሽኑ የሰው ሃብት ሥራ አመራር ዳይሬክተር ረዳት ኮሚሽነር ደርቤ ገቢሳ እንደገለጹት፤ ኮሚሽኑ ይጠቀምባቸው የነበሩ የደንብ ልብሶች በወንጀለኞች እጅ መግባታቸው ለመቀየሩ ምክንያት ሆኗል።         

በመሆኑም የፌዴራል ፖሊስ የበላይ አመራሮች ባስቀመጡት አቅጣጫ መሰረት እንዲቀየር ተደርጓል ብለዋል።     

ኅብረተሰቡን ከአዲሱ ልብስ ጋር በማስተዋወቅ የቀድሞውን የደንብ ልብስ ለብሰው ወንጀል የሚሰሩ ካሉ እንዲከላከል ማስቻልም ለደንብ ልብሱ መቀየር ሌላው ምክንያት ነው ብለዋል።     

ሕዝቡ በደንብ ልብሱ ላይ የሚቀመጡ ማዕረጎችን በአግባቡ እንደማያውቃቸው የጠቀሱት ረዳት ኮሚሽነሩ በአዲሱ የደንብ ልብስ በግልጽና በቀላሉ መለየት በሚያስችል መልኩ መቀመጣቸውን ገልጸዋል።

አዲሱ የደንብ ልብስ ሠራዊቱ ግዳጁን በተሻለ ደረጃ መፈጸም እንዲችል ለተለያየ የአየር ሁኔታ ጭምር ታሳቢ ተደርጎ የተዘጋጀ መሆኑንም ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም