የአገር ሕልውና ዘመቻውን የሚደግፍና የአሜሪካን ጣልቃ ገብነትን የሚቃወም ሠላማዊ ሠልፍ በዋሽንግተን ዲሲ እየተካሄደ ነው

ጥቅምት 29/2014 (ኢዜአ) የአገር ሕልውና ዘመቻውን የሚደግፍና የአሜሪካን ጣልቃ ገብነትን የሚቃወም ሠላማዊ ሠልፍ በአሁኑ ሠዓት ዋሽንግተን ዲሲ እየተካሄደ ይገኛል።

"በአገር ሕልውናና አንድነት አንደራደርም" በሚል መሪ ሀሳብ እየተካሄደ ያለው ሠላማዊ ሠልፍ በ'ሠላምና አንድነት ለኢትዮጵያ ግብረ ሃይል በዲሲ፤ በአገር ወዳድ ኢትዮጵያዊያንና የተለያዩ ተቋማት ትብብር የተዘጋጀ ነው።

በዋይት ሃውስ ፊት ለፊት እየተካሄደ በሚገኘው ሠላማዊ ሠልፍ "አሜሪካ የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት አክብሪ"፣ "አሜሪካ በኢትዮጵያ ላይ የምታደርገውን ጣልቃ ገብነት ታቁም"፣ "ኢትዮጵያ በራሷ ጉዳይ የሌሎችን ትዕዛዝ አትቀበልም"፣ "ኢትዮጵያን ከአጎዋ የማስወጣት ውሳኔ ስህተት ነው፤ የሚጎዳው ንጹሃን ዜጎችን ነው"፣ ኢትዮጵያ አሸናፊ የሆነቸው በአጎዋ ሳይሆን በአድዋ ነው"፣ "ሲኤንኤን በኢትዮጵያ ላይ የሚሰራውን ሀሰተኛ መረጃ ያቁም"፣ "ኢትዮጵያ ቅኝ ገዢዎችን አሸንፋለች አሁን ኒኦ-ኮሎኒያሊስቶችንም ታሸንፋለች" የሚሉ መልክቶች እየተላለፉ ነው።

በሰልፉ ላይ በርካታ ቁጥር ያላቸው በአሜሪካ የተለያዩ ግዛቶችና ከተሞች የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን እየተሳተፉ ይገኛሉ።

በሠላማዊ ሠልፉ ላይ ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም የህወሓት አሸባሪ ቡድን በፈጸመው ጥቃት በግፍ የተጨፈጨፉ የአገር መከላከያ ሠራዊት የሰሜን ዕዝ አባላት የሚዘከሩበት መርሃ ግብርም ይካሄዳል።

ሠልፈኞቹ የአገርን ሕልውና ለማስጠበቅ መስዋዕትነት በመክፈል ላይ የሚገኙ የመከላከያ ሠራዊት አባላትና ሌሎች የጸጥታ አካላት አጋርነታቸውንና ድጋፋቸውን እንደሚያሳዩም ተነግሯል።

አሜሪካ በኢትዮጵያ ላይ የምታደርገውን ያልተገባ ጫናና ጣልቃ ገብነት እንድታቆምና የተሳሳተ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲዋን እንድታጤን የሚያሳስቡ መልዕክቶች እንደሚተላለፉም ይጠበቃል።

በሠላማዊ ሠልፉ ላይ አሜሪካ ከኢትዮጵያ ላይ እጇን እንድታነሳ ጥሪ የሚያቀርብ ደብዳቤ ለዋይት ሃውስ እንደሚሰጥም ለማወቅ ተችሏል።

በአሜሪካ የዳያስፖራው ማኅበረሰብ ተወካዮችና የሃይማኖት አባቶችም ንግግር ያደርጋሉ ተብሏል።

በሌላ በኩል በቅርቡ የቨርጂኒያ ግዛት ገዢን ለመምረጥ በተካሄደው ምርጫ ትውልደ ኢትዮጵያዊያን የነበራቸውን ሚና ለዴሞክራቲክ ፓርቲ እንዲያውቁት እንደሚደረግ ኢዜአ ከሠልፉ አስተባባሪዎች ያገኘው መረጃ ያመለክታል።

የሪፐብሊካን ፓርቲ ዕጩው ግሌን ያንግኪን የዴሞክራቲክ ፓርቲ ዕጩን ቴሪ ማካውሊፍን አሸንፈው የቨርጂኒያ ግዛት ገዢ ሆነው መመረጣቸው ይታወቃል።

በምርጫው ትውልደ ኢትዮጵያዊያን ለሪፐብሊካኑ ዕጩ ድምጽ መስጠታቸውንና ይሄን ያደረጉበት ምክንያትም በስልጣን ላይ ያለው ዴሞክራቲክ ፓርቲ በአሜሪካ እየተከተለ ያለውን የተሳሳተ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ እንዲያጤነው ለማሳሰብ እንደሆነም ተገልጿል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም