ቀጥታ፡

የጎንደር ከተማና የባሶና ወራና ወረዳ ሴቶች ለዘማቾች የስንቅ ዝግጅት እያካሄዱ ነው

ጎንደር /ደብረ ብርሃን  ጥቅምት 29/2014 (ኢዜአ) ህልውና ዘመቻ እየተሳተፉ ላሉ መከላከያ ሰራዊትና ሌሎች የጸጥታ ሀይሎች እንዲሁም መርቀን ወደ ግንባር ለላክናቸው ልጆቻችን ስንቅ በማዘጋጀት ደጀንነታችንን እናጠናክራለን  ሲሉ የጎንደር ከተማ ሴቶች አስታወቁ፡፡

በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን የባሶና ወራና ወረዳ ሴቶችም ለክተት ጥሪው በስንቅ ዝግጅት ምላሽ እየሰጡ መሆናቸውን  ለኢዜአ ተናግረዋል።

በጎንደር ከተማ በህልውና ዘመቻው እየተሳተፉ ላሉ የመከላከያ ሰራዊትና ሌሎች የጸጥታ ሀይሎች እንዲሁም የክተት ጥሪን ተቀብለው ወደ ግንባር ለተሸኙ አካላት በህብረተሰቡ ተሳትፎ 50 ሚሊዮን ብር ግምት ያለው የስንቅ ዝግጅት እየተካሄደ ነው፡፡

በጎንደር ከተማው የቀበሌ 07 ነዋሪ ወይዘሮ አንሻ ሀሰን ለኢዜአ እንደገለጹት ህወሀት በከፈተው ወረራ ይበልጥ እየተጎዱ ያሉት ሴቶችና ህጻናት በመሆናቸው ጦርነቱ ፈጥኖ እንዲቋጭ የደጀንነት ሚናቸውን በሚገባ ይወጣሉ።

"በህልውና ዘመቻው እየተሳተፉ ላሉ የጸጥታ ሀይሎች እንዲሁም መስዋትነት ከፍለው ሃገር እንዲያስከብሩ መርቀን ወደ ግንባር ለላክናቸው ልጆቻችንና ወንድሞቻችን ስንቅ እያዘጋጀን ነው" ብለዋል፡፡

በአሸባሪው እየተፈፀመ ያለው ግፍ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ እንዲቆም አስፈላጊ ከሆነ ሴቶችም ወደ ግንባር ለመዝመት ዝግጁ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

"የምንሳሳላቸውን ልጆቻችንን፣ ወንድሞቻችንና የትዳር አጋሮቻችንን መርቅን ወደ ግንባር የሸኘነው ያለሀገር መኖር ስለማይቻል ነው'' ያሉት ደግሞ በከተማው የቀበሌ 06 ነዋሪ ወይዘሮ ታድፋለች ታምሩ ናቸው፡፡

ሴቶች በክተት ጥሪው ዳቦ ቆሎ፣ ኩኪስና በሶ በማዘጋጀት ለህልውና ዘመቻው መሳካት የድርሻቸውን እየተወጡ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በጎንደር ከተማ የእናታለም የሴቶች እድር አመራር ወይዘሮ ሀዲያ መሃመድ በበኩላቸው 150 ሴት የማህበሩ አባላት ስንቅ ለማዘጋጀት ገንዘብ ማዋጣታቸውን ተናግረዋል።

"አምስት ኩንታል በሶና አንድ ኩንታል ደረቅ ብስኩት በግንባር ለዘመቱ ወንድሞቻችን እያዘጋጀን ነው" ብለዋል፡፡

ለክተት ጥሪው ስኬታማነት በህብረተሰቡ ተሳትፎ 50 ሚሊዮን ብር የሚገመት የስንቅ ዝግጅት እየተካሄደ መሆኑን የገለፁት ደግሞ የከተማው ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ አቶ ዘውዱ ማለደ ናቸው።

ለሀገራዊ የክተት ጥሪ የህብረተሰቡ ምላሽ የሚያኮራ መሆኑን ገልጸው "ከስንቅ ዝግጅቱ በተጓዳኝ በጥሬ ገንዘብ 100 ሚሊዮን ብር የማሰባሰብ ስራ መጀመሩን አመልክተዋል፡፡

ከተማ አስተዳደሩ በክተት ጥሪው ወደ ግንባር ለላካቸው የሚሊሻና የፋኖ አባላት ግዳጃቸውን አጠናቀው አስኪመለሱ ድረስ የስንቅ ወጪያቸውን እንደሚሸፍን ታውቋል፡፡

በተመሳሳይ ዜና ለክተት ጥሪው በስንቅ ዝግጅት ምላሽ እየሰጡ መሆናቸውን በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን የባሶና ወራና ወረዳ ሴቶች ተናግረዋል።

በወረዳው የስንቅ ዝግጅት ሥራ ላይ እየተሳተፉ ካሉ ሴቶች መካከል ወይዘሪት ሰላም ከበደ አንዳለችው ሀገርና ህዝብን በመክዳት በሠራዊቱና በንጹሀን ዜጎች ላይ የግፍ በትሩን ያሳረፈውን ህወሓት ለመቅበር ሁሉም በሚችለው መሳተፍ አለበት።

የአካባቢው ሴቶች ጋር የክተት ጥሪን ተቀብለው ለሚዘምቱ ሚሊሻ፣ ተመላሽ የሠራዊት አባላትና ወጣቶች ስንቅ እያዘጋጁ መሆናቸውን ገልጻለች።

"አሸባሪው ህወሓት በጀግኖች አባቶቻችን ታፍራና ተከብራ የኖረች ኢትዮጵያን ለውጪ ጠላት አሳልፎ ለመስጠት የሚያደርገውን ጥረት ተባብረን ልናስቆመው ይገባል" ስትል ተናግራለች።

የሽብር ቡድኑ አባላት ሴቶችና ታዳጊ ህጻናትን አስገድደው እየደፈሩ መሆኑንና ይህም በዓለም አቀፍ ህግ እንደሚያስጠይቅ የገለጸችው ወይዘሪት ሰላም፣ አሸባሪውን ህወሀት ለማጥፋት በሚደረገው ጥረት ከስንቅ ዝግጅት ባሻገር በግንባር ለመዝመት ቁርጠኛ መሆኗን አረጋግጣለች።

"በሀገር ሉአላዊነትና በህልውናችን አንደራደርም፤ የሚከፈለውን የህይወት ዋጋም ቢሆን እንከፍላለን" ያሉት ደግሞ ሌላዋ የወረዳው ነዋሪ ወይዘሮ በልዩ አሰፋ ናቸው።

በስንቅ ዝግጅት የጀመሩትን የደጀንነት ሚና እንደሚያጠናክሩ ገልጸዋል።

በባሶና ወራና ወረዳ የብልጽግና ጽህፈት ቤት ሀላፊና የህልውና ዘመቻው የሎጅስቲክ ዘርፍ አስተባባሪ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ መሳይ መክብብ በበኩላቸው፣ ህዝቡ ለክተት ጥሪው ተግባራዊ ምላሽ እየሰጠ መሆኑን ገልጸዋል።

በአጭር ጊዜ ውስጥ ከወረዳው አርሶ አደሮች 908 ኩንታል እህል በማሰባሰብ ለዘማቾች በሶ፣ ዳቦ ቆሎ እና ሌሎች ደረቅ ምግቦች እየተዘጋጁ መሆናቸውን  አስታውቀዋል።።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም