ኢትዮጵያዊያን በአንድነት በመነሳት የሀገር ሉዓላዊነትን ማስከበር ይገባናል - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያዊያን በአንድነት በመነሳት የሀገር ሉዓላዊነትን ማስከበር ይገባናል
ጥቅምት 29/2014 (ኢዜአ) ኢትዮጵያዊያን እንደ ትናንቱ ሁሉ በአንድነት በመነሳት የሀገር ሉዓላዊነትን ማስከበር ይገባናል ሲሉ የ15ኛው የጉሚ በለል የውይይት ተሳታፊዎች አስገነዘቡ።
15ኛው ዙር "ጉሚ በለል" የውይይት መድረክ "የኦሮሞ ህዝብ ትግልና የአሸባሪው ህወሓት ወረራ" በሚል ርዕስ ዛሬ በፕሬዝዳንት ጽህፈት ቤት ተካሂዷል።
በክልሉ ፕሬዝዳንት ጽህፈት ቤት የሚዘጋጀው "ጉሚ በለል" የውይይት መድረክ በወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ ጉዳዩ በሚመለከታቸው ግለሰቦችና ምሁራን የሚካሄድ ነው።
የታሪክ ባለሙያ የሆኑት አቶ ከድር ማሞ ባቀረቡት የውይይት መነሻ ጽሁፍ በኢትዮጵያ የአገር ግንባታ ታሪክ ውስጥ የኦሮሞ ህዝብ ከሌሎች የኢትዮጵያ ልጆች ጋር በመሆን አኩሪ ድርሻ እንደነበረው አመልክተዋል።
ህዝቡ ለአገር ምስረታ ካበረከተው የላቀ ድርሻ በተጨማሪ የአገር ሉዓላዊነት ተከብሮ እንዲቀጥል መስዋዕትነት ሲከፍል መኖሩን ጠቁመው የአድዋና የሶማሌ ጦርነቶችን ለአብነት ጠቅሰዋል።
አሸባሪው ህወሀት ሀገሪቱን በበላይነት ባስተዳደረባቸው ባለፉት 27 ዓመታት የኦሮሞ ህዝብ ላይ አስከፊ ጭቆና ፈጽሞ እንደነበር ያወሱት አቶ ከድር ህዝቡ ከሌሎች የኢትዮጵያ ብሔሮች ጋር በመሆን ህወሀትን ወደ መቀሌ ማስገባቱን ተናግረዋል።
የስልጣን ጥመኛውና አገር አፍራሹ ህወሃት ላለፉት ሶስት ዓመታትም ህዝብን በስውር ሲያስገድልና ሲያፈናቅል መቆየቱ አልበቃ ብሎት አሁንም ሰይጠናዊ ተግባሩን አጠናክሮ በመቀጠል ህዝብን በግፍ እየማገደ መሆኑን አንስተዋል።
"አሸባሪው ህወሃት ለተሳሳተ ዓላማ ለጦርነት ከሚማግደው ህዝብ የበለጠ እኛ ኢትዮጵያዊያን ለአገር ሉዓላዊነትና ለትክክለኛ ዓላማ ተደራጅተን ጠላትን ለመጨረሻ ጊዜ መቅበር ይገባናል" ብለዋል።
"የአዲስ አበባ ከተማ ኮሚኒኬሽን ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ አብዲ ጸጋዬ በበኩላቸው ህወሃት የኦሮሞንም ሆነ መላውን የኢትዮጵያ ህዝብ በፖለቲካው አስሮናል፤ በኢኮኖሚው ለማኝ አድርጎናል፤ በማህበራዊውም ወግና ባህላችንን ቀምቶናል" ብለዋል።
"የኦሮሞ ህዝብ ያንን ሁሉ ግፍና መከራ ረስቶ ዛሬ በተላላኪዎቹ በኩል የአሸባሪው ተሸካሚ መሆን የሚችልበት ትከሻ አይኖረውም" ሲሉ አመልክተዋል።
"በሱማሌ ጦርነት ለአገር ክብር ጀብዱ ስንፈጽም ነበር" ያሉት ደግሞ የቀድሞ መከላከያ ሰራዊት የድጋፍና ልማት ማህበር የህዝብ ግንኙነት ሃላፊ መቶ አለቃ በቀለ በላይ ናቸው።
ትናንት ህይወታቸውን ለአገር ክብር የሰውና ነጻነትን ያወረሱን ጀግኖችን ማስታወስና ማክበር እንደሚገባ ያወሱት መቶ አለቃ በቀለ የኦሮሞ ህዝብ ከሌሎች ወንድም የኢትጵያ ህዝብ ጋር ሆኖ ወራሪውን በመደምሰስ የጀግንነት ታሪኩን ማደስ እንደሚገባው አስገንዝበዋል።
በውይይት መድረኩ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ተወካዮችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ታድመዋል።