ቀጥታ፡

ነገ የሚከበረው የአረፋ በዓል በሙስሊሙ ህብረተሰብ አንድነትና መቀራረብ የሚፈጠርበት እንዲሆን ተጠየቀ

አዲስ አበባ ነሀሴ 14/2010  የዘንድሮው የኢድ አል-አደሃ ወይም የአረፋ በዓል የሙስሊሙ አንድነትና መቀራረብ መሰረት የሚጣልበት ሆኖ ማለፍ እንደሚገባው የኢትዮጵያ ሙስሊም ተቋማዊ ለውጥ አንድነት ኮሚቴ አሳሰበ። ኮሚቴው በነገው እለት ኢትዮጵያን ጨምሮ በመላው ዓለም የሚከበረውን 1439 አመተ ህጅራ የኢድ አል-አደሃ በዓል በማስመልከት የእንኳን አደረሳችሁ መልእክት አስተላልፏል። የኮሚቴው ሰብሳቢ ተቀዳሚ ሙፍቲ ሼክ ኡመር ኢድሪስ እንዳሉት በመኮራረፍና በጥቃቅን አለመግባባቶች ተበታትኖ በየፊናው የሚከወን ስረዓተ ፀሎት ከእምነቱ አስተምህሮ እና ከኢድ በዓል አከባበር መርህ ጋር የሚቃረን ተግባር በመሆኑ ሊቆም ይገባዋል። መላው ሙስሊም ማህበረሰብ  በየአከባቢው አማካይ የሆነ አንድ ቦታ ላይ በመሰባሰብ የኢድ አል-አድሃ ስርዓተ ፀሎትንና ተያያዥ የበዓሉ ተግባራትን በጋራ መከወን እንዳለበት አሳስበዋል። ሙስሊሙ ማህበረሰብ በዓሉን ኢስላማዊ ስነ-ምግባርን በተላበሰ ወንድማማችነትና አንድነት መንፈስ ሊያከብረው እንደሚገባም አስገንዝበዋል። የኮሚቴው አባል የሆኑት ኡስታዝ አቡበከር አህመድ በበኩላቸው የኢድ አል-አድሃ በዓል አከባበር በአሁኑ ወቅት በአገር አቀፍ ደረጃ እየተካሄደ ካለው የመተሳሰብና የመተባበር ጅምር ብሄራዊ ጉዞን የሚያግዝ መሆን አለበት ብለዋል። በመሆኑም አዲስ አበባ ላይ ያለው ሙስሊም በአዲስ አበባ ስቴዲየም፤ በሌሎች ከተሞች ያሉ ደግሞ በአንድ አማካይ ቦታ ላይ ተሰባስበው በዓሉን አብሮነትንና አንድነት ስሜት እንዲያከብሩት ጠይቀዋል። የኢድ አል-አድሃ (አረፋ) በዓል ነብዩላህ አብርሃም ልጁ ይስሃቅን እንዲያርድ ከፈጣሪ የቀረበለትን መለኮታዊ ትእዛዝ ለመፈፀም ያሳየውን  ቁርጠኝነት ለመዘከር በየዓመቱ የሚከበር ታላቅ በዓል ነው። በዚህም ምክንያት በበዓሉ እርድ መፈፀም የሚወደድ ተግባር በመሆኑ ሙስሊሙ ማህበረሰብም በሚችለው አቅም እርድ በማድረግ ከቤተሰብ፣ ከጎረቤትና ችግርተኛ ወገኖቹ ጋር ያከብራል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም