ቀጥታ፡

የአገር ሉዓላዊነትን አደጋ ላይ የሚጥል የጥፋት ተልእኮ የያዘ ጥምረት ፍፁም ተቀባይነት የለውም

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 29 ቀን 2014 (ኢዜአ) የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት አደጋ ላይ የሚጥል የጥፋት ተልእኮ የያዘ ማንኛውም አይነት ጥምረት ፍፁም ተቀባይነት የሌለው መሆኑን የኢትዮጵያ ፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ገለጻ።

በኢትዮጵያ ላይ እየደረሰ ያለው ግፍና ጫናም ለምስራቅ አፍሪካ ቀጣና ጭምር የሚተርፍ መሆኑን ገልጿል።


የኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ወቅታዊ አገራዊ ጉዳዮችን አስመልክቶ መግለጫ ሰጥቷል።

በመግለጫው የኢትዮጵያ ሕዝብ ራሱ መርጦ የሚያቆመውን እንጂ ከአገር ውስጥም ሆነ ከውጪ "ተጠፍጥፎ የሚመጣለትን አሻንጉሊት መንግስት" በታሪክ ተቀብሎ አያውቅም፣ ዛሬም አይቀበልም ብሏል።

የምክር ቤቱ ሰብሳቢ ዶክተር ራሔል ባፌ፤ የአንዳንድ የአገራት ሚዲያዎች፣ የኢትዮጵያ መንግስታት ያለቀለትና የተበታተነች አስመስለው እየቀረቡ ነው ብለዋል።

በሰሜን አሜሪካ ራሳቸውን የፌዴራሊስት /ኮንፌዴራሊስት/ ጥምረት በማለት ኢትዮጵያን ለማፍረስ በሚል መመስረታቸውን መስማታቸውንም አንስተዋል።

በጥምረቱ በኢትዮጵያ ፓርላማ በአሸባሪነት በተፈረጀው ሕወሓት አቀናባሪነት ሲንደፋደፍ የታዩ ግለሰቦች ማየት ያሳዝናል ያሉት ሰብሳቢዋ የጥፋት ተልእኮ የያዘ ማንኛውም አይነት ጥምረት ፍፁም ተቀባይነት የለውም ብለዋል።

በዚህ ፈታኝ ወቅት ሁሉም ዜጋ በተለይም የቀድሞ የሰራዊት አባላትና የውትድርና ስልጠና ያላቸው ዜጎች ሁሉ ኢትዮጵያ ለምትጠይቀው ሁሉ ምላሽ ለመስጠት እንዲዘጋጁ ጠይቀዋል።

መግለጫው መንግስት በጦርነቱ ምክንያት የተፈናቀሉ ዜጎችን መልሶ ለማቋቋም ቅድሚያ እንዲሰጥ፣ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ንጹሃን ዜጎች እንዳይገለቱም ጥንቃቄ እንዳይለይ ጠቁመዋል።

መንግስት የአገራዊ መግባባት መድረኩን አፋጥኖ ታሪካዊ ኃላፊነቱን ይወጣም ተብሏል በመግለጫው።

የምክር ቤቱ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል አቶ የሺዋስ አሰፋ በበኩላቸው በምዕራባውያን በኩል በኢትዮጵያ ላይ በጭፍን ጥላቻ ጫና እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል።

ጫናው የሚያስከትለው ችግር ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ለምስራቅ አፍሪካ ጭምር የሚተርፍ መሆኑን ሊያውቁ የገባልም ነው ያሉት።

ወቅታዊ ሁኔታውን ተገን በማድረግ ጸረ ኢትዮጵያ እንቅስቃሴ እያደረጉ ያሉ ግለቦችም ከድርጊታቸው መቆጠብ እንዳለባቸው ገልፀጸዋል።

ኢትዮጵያን የምታክል የነጻነት ተምሳሌት የሆችን አገር ለማፍረስ ጥረት ማድርግ ፍፁም ተቀባይነት የለውም ብለዋል።

የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት 53 የፖለቲካ ፓርቲዎችን በአባልነት ያቀፈ መሆኑ ይታወቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም