የምዕራባዊያንና የዓለም አቀፍ ተቋማት አድሏዊ አቋም መታረም አለበት - ኢዜአ አማርኛ
የምዕራባዊያንና የዓለም አቀፍ ተቋማት አድሏዊ አቋም መታረም አለበት
ጥቅምት 29/2014 (ኢዜአ) ምዕራባዊያን መንግስታትና ዓለም አቀፍ ተቋማት በኢትዮጵያ ጉዳይ የያዙት አድሏዊ አቋም ያልተገባና ሊታረም የሚገባው መሆኑን በተለያዩ የዓለም ክፍሎች የሚገኙ የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ምሁራን ገለጹ።
ምሁራኑ የኢትዮጵያ ወዳጆች ከኢትዮጵያ ጎን የሚቆሙበት ጊዜ አሁን ነው ብለዋል።
በሰሜን አሜሪካ፣ አውሮፓ፣ አውስትራሊያና አፍሪካ የሚገኙ 70 የሚጠጉ የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ምሁራን ስብስብ በኢትዮጵያ ወቅታዊ ሁኔታ ላይ ባወጡት መግለጫ የህወሓት ቡድን ከስልጣን ከተወገደ በኋላ በነበሩት ሁለት ዓመታት አገሪቷ በከፍተኛ ሁኔታ የሳይበር ጦርነት ተከፍቶባት እንደነበር ገልጸዋል።
አሁን በኢትዮጵያ ባለው ግጭትም የሳይበር ጦርነቱ በድጋሚ መጀመሩንና ሐሰተኛ መረጃን እንደ ዋና መሳሪያ በመጠቀም ኢትዮጵያን ለመበታተን ሙከራ እየተደረገ መሆኑን አመልክተዋል።
ዳያስፖራዎች ምሁራን በቅርብ ጊዜ ውስጥ የዚህን ያህል ከፍተኛ የፕሮፓጋንዳ ዘመቻ ተከፍቶ እያውቅም ነው ያሉት።
አሸባሪው የህወሓት ቡድን በሚፈበርካቸው ሀሰተኛ መረጃዎችና በሚያሰራጨው ፕሮፓጋንዳ ዓለም አቀፉን ማኅበረሰብ እያሳሳተ መሆኑን ተናግረዋል።
የምዕራባዊያን መገናኛ ብዙሃንም ውሸቱን በማስተጋባት የጋዜጠኝነትን መርህ በጣሰ መልኩ ረሃብ ለጦር መሣሪያነት ውሏል፣ የዘር መጥፋትና በተደራጀ መልኩ የአስገድዶ መድፈር ጥቃቶች ተፈጽሟል ሲሉ መዘገባቸውን አውስተዋል።
ምዕራባዊያኑ የህወሓት ቡድን ስልጣን ላይ በነበረባቸው ሶስት አስርት ዓመታት በተቀናጀና መጠነ ሰፊ በሆነ መልኩ ሲፈጽማቸው ለነበሩ የሠብዓዊ መብት ጥሰቶች ዝምታን መርጠው፤ በሰሜን ኢትዮጵያ ባለው ግጭት የኢትዮጵያን መንግስት የሠብዓዊ መብት ጥሰት ተጠያቂ ለማድረግ መሞከራቸው እውነታውን ለመሸፈን የሚያደርጉት ጥረት ማሳያ መሆኑንም ነው ምሁራኑ የገለጹት።
አገራት በተዛቡ ዘገባዎችና በተቀናጁ የሀሰተኛ መረጃ ዘመቻዎች ተነስተው ኢትዮጵያ ላይ ማዕቀብን ጨምሮ የተለያዩ እርምጃዎች መውሰዳቸው ተገቢነት የሌለው ነው ብለዋል።
አሜሪካ ኢትዮጵያን የብሔራዊ ደህንነት ስጋት ብላ በመፈረጅ እና በፕሬዚዳንት ጆ ባይደን ትዕዛዝ ከአሜሪካ ከቀረጥ ነጻ የንግድ ዕድል /አጎዋ/ ለማስወጣት መወሰኗ የዚሁ ማሳያ መሆኑን ነው ዳያስፖራ ምሁራኑ በመግለጫቸው ያመለከቱት።
"የኢትዮጵያ መንግስት ዘር ማጥፋት ፈጽሟል እንዲሁም ረሃብን ለጦር መሳሪያነት ተጠቅሟል" ተብሎ ሲቀርቡበት የነበሩት ክሶችን ውድቅ ያደረገው የኢትዮጵያ ሠብዓዊ መብቶች ኮሚሽንና የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሠብዓዊ ጉዳዮች ከፍተኛ ኮሚሽነር ቢሮ የጋራ ሪፖርት ከቀናት በፊት መውጣቱን አስታውሰዋል።
የምዕራባዊያን መገናኛ ብዙሃን ሪፖርቱን ከእነሱ ዘገባና ፍላጎት ጋር የሚቃረን በመሆኑ ጆሮ ዳባ ልበስ ማለታቸውን አመልክተዋል።
መገናኛ ብዙሃኑ ትኩረት ባልሰጡት በዚህ ሪፖርት የህወሓት ቡድን በሰሜን ዕዝ ላይ በፈጸመው ጥቃት ምክንያት ጦርነቱ መጀመሩንና የኢትዮጵያ ጸጥታ ሃይል ወደ እርምጃ መግባቱን በግልጽ ማስቀመጡን ነው የዳያስፖራ ምሁራኑ የገለጹት።
"ምዕራባዊያን ታይቶ በማይታወቅ መልኩ በጭፍንነት ለሕወሓት ቡድን እየሰጡት ያለው ድጋፍ ለጦርነቱ ተባብሶ መቀጠል ምክንያት ሆኗል" ብለዋል ምሁራኑ።
ምዕራባዊያኑ ለጦርነቱ መጀመር ተጠያቂ የሆነውንና በአፋርና አማራ ክልሎች አሰቃቂ ግድያና ከፍተኛ ዘረፋ እየፈጸመ ስላለው የህወሓት ቡድን ጆሮ መስጠት አለመፈለጋቸውንም ጠቁመዋል።
አሸባሪው ቡድን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የእርዳታ ተሽከርካሪዎችን ለጦርነት እየተቀመ ባለበት ሁኔታ የኢትዮጵያን መንግስት እርዳታ እንዳይሰጥ አግዷል በማለት ክስ እየቀረቡ ይገኛሉ ነው ያሉት።
"ኢትዮጵያን ለማዳከም የምዕራባዊያኑ አስደንጋጭ በሆነ መልኩ እያሳዩት ያለው አድሏዊነትና ግልጽ ጣልቃ ገብነት ጦርነቱ እንዲያበቃ ገንቢ ሚና የሌለው እንደሆነም አመልክተዋል ምሁራኑ፤
እነዚህ ምዕራባዊያን ለአገር ደህንነት የሚጨነቁ መስለው በሊቢያና በሌሎች አገራት የፈጸሙት አሳዛኝ ድርጊት ትምህርት የሰጣቸው አይመስልም ሲሉም ገልጸዋል።
አሸባሪው ህወሓት የፈጸማቸውን ጥሰቶችና ድርጊቶችን የሚያሳየው የሠብዓዊ መብት ሪፖርትና ሌሎች ከበቂ በላይ ማስረጃዎች እያሉ ምዕራባዊያኑ በዴሞክራሲያዊና በሕጋዊ መንገድ የተመረጠውን መንግስት ለማዳከም እያደረጉት ካለው ጥረት እጃቸውን አለመሰብሰባቸው ተቀባይነት የሌለው መሆኑን ምሁራኑ አስታውቀዋል።
የኢትዮጵያ መንግስት በሁሉም አቅጣጫ የተቀናጀ የፕሮፓጋንዳ ጦርነት እንደከፈተበትም ነው ምሁራኑ በመግለጫቸው የጠቆሙት።
የዳያስፖራ ምሁራኑ የምዕራባዊያን መንግስታትና ዓለም አቀፍ ተቋማት መንግስት ለኢትዮጵያና ለኢትዮጵያዊያን ፍላጎት ሲባል "ከከሃዲው ቡድን" ጋር ያለው ጦርነት እንዲያበቃ እያደረገ ያለውን ጥረት በቅንነት በመረዳት ያላቸውን አድሏዊና ሚዛናዊ ያልሆነ አቋም እንዲያስተካክሉም ጥሪ አቅርበዋል።
የኢትዮጵያ ሕዝብ ህወሓትን ቡድን አልፈልግህም ብሎ ከስልጣን ማውረዱንና ብሩህ ተስፋ በመሰነቅ አዲስ መንግስት መምረጡን ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ እንደ ሁልጊዜው ታሸንፋለች ያሉት ምሁራኑ የኢትዮጵያ ወዳጆች ከኢትዮጵያ ጎን እንዲቆሙም ጥሪ አቅርበዋል።
.