ሰባተኛው ዙር የይቆጥቡ ይሸለሙ የማበረታቻ ሽልማት ዕጣ ወጣ - ኢዜአ አማርኛ
ሰባተኛው ዙር የይቆጥቡ ይሸለሙ የማበረታቻ ሽልማት ዕጣ ወጣ
አዲስ አበባ ነሃሴ 14/2010 የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሰባተኛ ዙር የይቆጥቡ ይሸለሙ የቁጠባ ፕሮግራም የማበረታቻ ሽልማት ዕጣ ወጣ። ከታህሳስ 23 እስከ ሰኔ 23 ቀን 2010 ዓ.ም ድረስ ሲካሄድ የቆየው ይቆጥቡ ይሸለሙ የቁጠባ ማበረታቻ ሽልማት የዕጣ አወጣጥ ሥነ-ስርዓት ዛሬ በብሄራዊ ሎተሪ አዳራሽ ተካሂዷል:: በአንደኛ ዕጣ ሦስት የመኖሪያ ቤቶችን የሚያስገኙ የዕጣ ቁጥሮች ዕድለኞች በጅማ፣ በደሴና በመቀሌ የሚገኙ የባንኩ ደንበኞች ሆነዋል። በሁለተኛ ዕጣ 15 ባለ ሁለት ሺህ ሲሲ መለስተኛ የህዝብ ማመላለሻ ተሽከርካሪዎች፣ በሦስተኛ ዕጣ 15 ባለ ሦስት እግር ተሽከርካሪዎች፣ በአራተኛ ዕጣ 15 ላፕቶፕ ኮምፒዩተሮች እና ሦስት ሺህ ስማርት የሞባይል ቀፎዎች ለዕድለኞች ወጥተዋል:: የባንኩ የህዝብ ግንኙነት ሥራ አስኪያጅ ወይዘሮ ብሌን ኃይሉ እንደገለጹት የባንኩ የቁጠባ ፕሮግራም ማበረታቻ ሽልማት የደንበኞችን ቁጥር እና የተቀማጭ ሂሳብን ለማሳደግ ጉልህ አስተዋጽኦ እያበረከተ ይገኛል።