ሰርጎ ገቦችን አድኖ በመያዝ ለመንግስት እያስረከብን ነው -የአጣየና አካባቢው ወጣቶች

118

ደብረ ብርሃን (ኢዜአ) ጥቅምት 29/2014 ጠላት ሰርጎ ሊገባባቸው የሚችሉ በሮችን ከመጠበቅ ባሻገር የአሸባሪ ተላላኪዎችን አድኖ በመያዝ ለመንግስት እያስረከቡ መሆናቸውን ኤፈራታና ግድም ወረዳ የአጣየ ከተማ ወጣቶች አስታወቁ።

የአጣየ ከተማ ነዋሪ ወጣት በላቸው ትዜ ለኢዜአ እንደገለጸው አሸባሪው ህወሓት ኢትዮጵያን ለማፍረስ ከሸኔ ጋር በመተባበር የጀመረው እኩይ ተግባር እንዳይሳካ ተደራጅተው የበኩላችውን እየተወጡ ነው።

የሀገር እድገት፣ ሰላምና የህዝቦች አንድነት እንዳይረጋገጥ የሚሰሩ የባዕዳን ሀገር ተላላኪዎችን ለመቅበር ከመከላከያ ሠራዊት፣ ከአማራ ልዩ ሀይልና ከፋኖ አባላት ጋር በትብብር እየሰሩ መሆኑን ገልጿል።

"አሁን ላይ ወጣቶች ተደራጅተን ጠላት ሰርጎ ሊገባባቸው የሚችሉ በሮችን ከመጠበቅ ባሻገር ተላላኪዎችን አድኖ በመያዝ ለመንግስት እያስረከብን ነው" ብለዋል ።

የጀግኖች አባቶቻችንን የአድዋ ድልን ህወሓትንና ሸኔን በመደምሰስ ለመድገም ዝግጁ መሆኑን የገለጸው ደግሞ ሌላው የከተማው ነዋሪ ወጣት ጀማል መሀመድ ናቸው።

"ሸኔ ከዚህ በፊት በአጣየ ከተማ ላይ ያደረሰው ጥቃት ዳግም እንዳይፈጸም ብቻ ሳይሆን ጠላቶቻችንን በተባበረ ክንድ ለመደምሰስ በቁርጠኝነት ተነስተናል" ብላል።

የኤፍራታና ግድም ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ሰለሞን አልታየ በበኩላቸው የትህነግ ወራሪ ሀይልና የሸኔ አባላትን ለመከላከል ከአጎራባች ወረዳ አመራሮችና ማህበረሰብ ጋር በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን ተናግራዋል።

"ሸኔ ለኦሮሞ ጭቁን ህዝብ የሚታገል መስሎ የህወሓት አጥፊ ቡድን ተልእኮን ለማሳካት እየሰራ መሆኑን የኦሮሞ ህዝብ ጠንቅቆ በማወቁ ከእኛ ጋር በመናበብ እየሰራን ነው " ብለዋል።

የአጣየ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ አገኘሁ መክቴ በበኩላቸው "የአሸባሪዎቹ ተላላኪዎች ወደ ከተማዋ ለመግባት ቢሞክሩም በህዝብ ጥቆማና በወጣቶች ቅንጅት እየተለቀሙ ነው" ብለዋል።

በአጣየ ከተማ በአሁኑ ወቅት ምግብ ቤቶችና ሱቆች አገልግሎት እየሰጡ መሆኑን የገለጹት ከንቲባው "የህዝብና የሃገር ጠላቶችን ባሉበት በመደምሰስ ሰላማዊ እንቅስቃሴ ተጠናክሮ ይቀጥላል" ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም