የመለስ ሌጋሲና የኢትዮጵያ ህዳሴ ጉዞ ” በሚል መሪ ሃሳብ የተዘጋጀ ሀገር አቀፍ የውይይት መድረክ ተካሄደ - ኢዜአ አማርኛ
የመለስ ሌጋሲና የኢትዮጵያ ህዳሴ ጉዞ ” በሚል መሪ ሃሳብ የተዘጋጀ ሀገር አቀፍ የውይይት መድረክ ተካሄደ
መቀሌ ነሀሴ 14/2010 ስድስተኛው ዓመት የዝክረ መለስ መታሰቢያን ምክንያት በማድረግ የተዘጋጀ ሀገር አቀፍ የውይይት መድረክ በመቀሌ ከተማ ተካሄደ፡፡ "የኢትዮጵያ የህዳሴ ጉዞና የመለስ ሌጋሲ " በሚል መሪ ሀሳብ በተዘጋጀው በዚሁ መድረክ የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር ደብረፅዮን ገብረሚካኤል በዚህ ወቅት እንደገለጹት፣ ባለፉት 27 ዓመታት የሀገሪቱ ብሔሮች፣ብሔረሰቦችና ህዝቦች መብትና እኩልነት ተከብሯል፡፡ ፖለቲካወዊ፣ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ለውጦች ተመዝግበዋል። "አቶ መለስ ዜናዊ ያስቀመጡትን ራእይ ተግባራዊ ለማድረግ ከከፍተኛ አመራሩ ጀምሮ ቁርጠኛ መሆን ይኖርበታል፤ ለጋሲያቸው ለማስቀጠል ቃላችን ልናድስ ይገባል "ብለዋል። በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግስት ተጠሪ ሚኒስትር አቶ አስመላሽ ወልደስላሴ በውይይት መድረኩ ባቀረቡት የመነሻ ጽሁፍ ላይ እንዳሉት፣አቶ መለስ ለሀገሪቱ ህዳሴ እውን መሆን ያበረከቱት አስተዋፅኦና የተመዘገቡ ለውጦች ታላላቅ ናቸው ። "ባለፉት 27 ዓመታት በሀገሪቱ የተካሄዱ ፖለቲካዊ፣ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ እንቅስቃሴዎች ሃሳብ ከማመንጨት፣ ወደ ፖሊሲና ወደ ተግባር ከመቀየር አንፃር የታጋይ መለስ ድርሻ የጎላ ነበር "ብለዋል። አቶ መለስ ከትጥቅ ትግሉ ጀምሮ ያካባቱዋቸውን አቅሞችን በመጠቀም የቀየሷዋቸው ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች ለህዝብ ካላቸው ጠቀሜታ በመገንዘብ እንደነበርም አውስተዋል። "ኢህአዴግ በተለያዩ መድረኮች የሚያጋጥሙትን ችግሮች ለመፍታት የአቶ መለስ ዜናዊ በሳል አመራርና አርቆ አስተዋይነት ከፍተኛ ነበር" ብለዋል። ህዝቡ ያነሳቸው የነበሩት የመልካም አስተዳደርና ሌሎች ችግሮች ለመፍታት አመራሩ በፍጥነት ካልሮጠ ከተራራ የሚወርደው ናዳ ይደርስበታል ማለታቸው አስታውሰው፣አሁን የሆነውም ይህንኑ መሆኑን አቶ አስመለሽ ተናግረዋል። አቶ መለስ በአገራችን ብቻ ሳይሆኑ በአፍሪካና በተለያዩ የአለም መድረኮች የአፍሪካን ህዝቦች ጥቅም የሚያስከብሩ ክርክሮች በማድረግ እንደሚታወቁም አብራርተዋል። የመቀሌ ዩኒቨርስቲ መምህር የሆኑት ረዳት ፕሮፌሰር መረሳ ፀሐዬ " የብሄሮችና ብሄረሰቦች እኩልነት፣የሀገር አንድነትና የአዲሱ ትውልድ ሚና" በሚል ፅሁፍ አቅርበዋል፡፡ በዚሁ ጽሁፋቸው " አዲሱ ትውልድ የመለስና የትግል አጋሮቻቸውን መልካም ስራዎችን ወደ ላቀ ደረጃ እንዲሸጋገሩ በአዲስ መንፈስና በአንድነት መስራት ይገበዋል" ብለዋል። ከመድረኩ ተሳታፊዎች መካከል የትግራይ የመለስ ስራ አመራር ሰልጣኝ አቶ ንጉሴ ሙዘይ እንደገለጹት፣ ከአቶ መለስ ህዝባዊነትና የዓላማ ፅናትን መማራቸውን ተናግረዋል። አደራ ተረካቢ ወጣቶች በመሆናቸው ከአቶ መለስና የትግል አጋሮቻቸው ብዙ የሚማርባቸው ጉዳዩች እንዳሉ የተናገረው ደግሞ በመቀሌ ዩኒቨርስቲ የህክምና ትምህርት ክፍል ተማሪ መብራህቶም የዕብዮ ነው። " ያለፈው ትውልድ የራሱን መልካም ስራ ሰርቶ አልፏል፤ አሁን እኛ ወጣቶች የኢትዮጵያን አደራ ተቀብለን የምናስኬደው እኛ ነን" ብሏል፡፡ "አቶ መለስ የሴቶችን እኩልነት እንዲከበርና አቅማቸው እንዲጎለብት ያደረጉት አስተዋፅኦ ወጣቱ ትውልድ እንዲያስቀጥለው የውይይት መድረኩ አቅም ይሆናል " ያሉት ደግሞ ወይዘሮ እሌኒ አስመላሽ የተባሉት ተሳታፊ ናቸው፡፡ በውይይት መድረኩ የኢህአዴግ የቀድሞና የክልሉ ከፍተኛ አመራሮች፣ የሃገር መከላከያ ሰራዊት፣ የመቀሌ ዩኒቨርስቲ ምሁራን፣ የመለስ ዜናዊ ስራ አመራር ሰልጣኞችና የከተማው ነዋሪዎች ተወካዮች ተሳትፈዋል።