የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በአማራ ክልል ለተፈጠረው ለሰብዓዊ ቀውስ ድጋፍ እንደሚያደርግ አስታወቀ - ኢዜአ አማርኛ
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በአማራ ክልል ለተፈጠረው ለሰብዓዊ ቀውስ ድጋፍ እንደሚያደርግ አስታወቀ
ባህር ዳር (ኢዜአ) ጥቅምት 28/2014በአማራ ክልል አሸባሪው ህወሓት በፈጸመው ወረራ ለተፈጠረው ሰብዓዊ ቀውስ አስፈላጊውን ድጋፍ ለማድረግ እየሰራ መሆኑን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት አስታወቀ።
የድርጅቱ ተወካዮች ከአማራ ክልል ከፍተኛ ባለስልጣናት ጋር በክልሉ በተፈጸመው ወረራ፣ በደረሰው ሰብዓዊ ቀውስና ለተጎጂዎች የምግብ እህል በሚደርስበት ሁኔታ ላይ ዛሬ በባህር ዳር ከተማ መክረዋል።
በኢትዮጵያ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብዓዊ ድጋፍ አስተባባሪ ዳይሬክተር ዶክተር ካትሪና ሮሲ በውይይቱ ላይ እንዳሉት፣ ግጭቱ እየተባባሰ በመምጣቱ የተፈናቃዮች ቁጥር በየጊዜው እየጨመረ ስለመሆኑ ግንዛቤ ተይዟል።
"ዛሬ እዚህ የመጣንበት ዋና ምክንያት የሚፈናቀሉ ዜጎች የሚደርስባቸውን ሰብዓዊ ቀውስ ለመቀነስ በሚያስችል መልኩ በመምከር የጋራ መግባባት ፈጥረን ወደ ሥራ ለመግባት ነው" ብለዋል።
"ስለ ሰብዓዊ ድጋፍ ስናወራ ህይወት ስላማዳን እንጂ ወራትና ዓመታት ስለሚወስደው የልማት ጉዳይ አይደለም" ያሉት ዶክተር ካትሪን፣ "ጊዜ የማይሰጠውን ችግር ለማስወገድ በጋራ መረባረብ አለብን" ብለዋል።
በግጭቱ ለተፈናቀሉ ዜጎች ድጋፍ እንዲውል 7 ሚሊዮን ዶላር የሚጠጋ ገንዘብ ለኢትዮጵያ ሰብዓዊ ድጋፍ ማዕከል መለገሱንም አስታውቀዋል።
በዓለም ምግብ ፕሮግራም ካንትሪ ዳይሬክተር ዶክተር ስቴቭ ዌቭ በበኩላቸው እንዳሉት በአማራ ክልል በወረራ ውስጥ ለሚገኙ ዜጎች የምግብ እህል የማድረሱ ስራ የበርካታ አካላትን ፈቃደኝነት ይጠይቃል።
በደሴና ኮምቦልቻ መጋዘኖች ከ70 ሺህ በላይ ሜትሪክ ቶን የምግብ እህል መኖሩን ጠቁመው፣ እህሉን በወረራ ወደ ተያዙ አካባቢዎች ለማሰራጨት ተደጋጋሚ ሙከራ ቢያደርግም እንዳልተቻለ ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ መንግስት በሚቆጣጠራቸው አካባቢዎች ለተፈናቃዮች የምግብ ድጋፍ ማድረስ ቀላል መሆኑን ተናግረው፣ "ህወሓት በያዛቸው ዞኖችና ወረዳዎች ግን ድጋፉን ለማድረስ የትራንስፖርት፣ የደህንነትና ሌሎች ችግሮች አጋጥመዋል" ብለዋል።
ምግብ እህል ቢኖርም የሚደርስበት ሁኔታ ካልተመቻቸ ዜጎችን ከገጠማቸው ችግር ማውጣት እንደማይቻል የገለጹት ዶክተር ስቴቬ፣ "እነዚህን ችግሮች ለመፍታት ተቀራርቦ መስራት አማራጭ የለውም" ብለዋል።
የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር ይልቃል ከፍአለ በበኩላቸው በሰጡት ማብራሪያ አሸባሪው ህወሓት በፈጸመው ወረራ ለችግር የተጋለጡ ንጹሃን ዜጎችን ለመደገፍ ረጅ ድርጅቶች ፈጥነው እንዲገቡ ጠይቀዋል።
በክልሉ ስድስት ዞኖች በሙሉና በከፊል በወረራ ውስጥ መሆናቸውን የተባበሩት መንግስታት ሊያውቅ እንደሚገባ የገለጹት ዶክተር ይልቃል፣ "በእነዚህ አካባቢዎች ተከታታይና ሁሉን አቀፍ ድጋፍ ማድረግ ሃላፊነትን መወጣት መሆኑን ገልጸዋል።
ዓለም አቀፍ ድርጅቶች የምግብ ድጋፍ ለማድረግ በሚያደርጉት እንቅስቃሴ የሚገጥማቸውን ችግር ለመፍታት የክልሉ አስተዳደር ከምንጊዜውም በላይ ዝግጁ መሆኑን አረጋግጠዋል።
በእዚህም ችግሮችን ለመለየት፣ የመፍትሄ አቅጣጫዎችን ለማስቀመጥ፣ በአፈጻጸም የገጠሙ ድክመቶችን ለማረምና ጠንካራ ጎኖችን ለማስቀጠል ተከታታይነት ያለው የውይይት መድረክ አስፈላጊ መሆኑን ተናግረዋል።
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ተወካዮችም ከውይይቱ በኋላ በባህር ዳር ከተማ ዘንዘልማ የሚገኘውን ጊዜያዊ መጠለያ ጣቢያ ተገኝተው ተፈናቃዮች ያሉበት ሁኔታን ተመልክተዋል።
በአማራ ክልል አሸባሪው ህወሓት በያዛቸው አካባቢዎች ከ6 ሚሊዮን በላይ ህዝብ በችግር ውስጥ እንደሚገኝ ለውይይት መነሻ ከቀረበው ጽሁፍ መረዳት ተችሏል።