ቀጥታ፡

በመከባበርና በአንድነት የማናሸንፈው ምድራዊ ኃይል አይኖርም

ሀዋሳ ጥቅምት 28/2014 ዓ.ም /ኢዜአ/ በመከባበርና በአንድነት ከዘለቅን የማናሸንፈው ምድራዊ ኃይል እንደማይኖር አድዋና ካራማራ ምስክሮች መሆናቸው የስልጤ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አሊ ከድር ገለጹ፡፡

የዞኑ ሕዝብ በዛሬው ዕለት ለሕልውና ዘመቻው ስኬት 10 ሚሊዮን ብር የሚገመት ድጋፍ ማድረጉንም አስታውቀዋል ፡፡
በዞኑ የወራቤ ከተማና አካባቢው ነዋሪዎች ለሀገር መከላከያ ሠራዊት አጋርነታቸውን ለማሳየትና አሸባሪው ህወሓት ከውስጥና ከውጭ ጠላቶች ጋር በመሆን ሀገር ለማስፍረስ እየፈፀመ ያለውን እኩይ ተግባር ወራቤ ከተማ ባካሂዱት ሕዝባዊ ሰልፍ አወገዙ።

ዋና አስተዳዳሪው አቶ አሊ ከድር በዚሁ ጊዜ እንዳሉት በመከባበር አንድነታችን ጠብቀን ህብረታችንን ካጠናከርን የማናሸንፈው ምድራዊ ኃይል እንደማይኖር የአድዋና ካራማራ የድል ታሪኮች ህያው ምስክሮች ናቸው።

በዞኑ በተካሄደ ህዝባዊ ሰልፍና ድጋፍ ለሀገር መከላከያ ሰራዊት ከ10 ሚሊዮን ብር በላይ በአይነትና በጥሬ ገንዘብ መሰብሰብ ተችሏል ፡፡    

በኢትዮጵያ ለ27 ዓመታት ተንሰራፍቶ የቆየው ከፋፋይና ሀገር አፍራሽ የፖለቲካ ሥርዓት በህዝባዊ እምቢተኝነት ከተገረሰሰ በኋላ በሀገዊ ለውጡ ተጨባጭ ውጤት ተመዝግቧል፤ እየተመዘገበም ነው።

ከሀገዊ ለውጡ በኋላ በለውጡ የተመዘገቡት አያሌ ተስፋ ሰጪና አበረታች ተጨባጭ ውጤቶች ግን ለአሸባሪው ህወሓትና አጋዦቹ አልተዋጠላቸውም ብለዋል።

ከሀዲውና አሸባሪው  ህወሓት ኢትዮጵያን እንደ መዥገር ተጣብቶ ደሟን ሲመጥ የኖረ በመሆኑ እንዳሻኝ እየዘረፍኩ ካልኖርኩ ሲኦልም ቢሆን ወርጄ አፈርሳታለሁ የሚል ግልፅ አቋም ሰርቷል፤ እየሰራም ነው።

ለዚህ እኩይ ዓላማው በሀገር መከላከያ ሠራዊት የሰሜን ዕዝን ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም በድንገት በማጥቃት ታሪክ ፈጽሞ የማይዘነጋው የሀገር ክህደት ወንጀል ፈጽሞ ጦርነት ማወጁን ጠቅሰዋል።

ሀገርን ለማፍረስ ከውስጥ ባንዳዎችና ከውጭ ታሪካዊ ጠላቶቿ ጋር ያለተቀደሰ “ ሀራም ” ጋብቻ የፈፀመው አረመኔ ህወሓት በአሁኑ ወቅት ዜጎችን ኢ-ሰብዓዊ ድርጊቶችን እየፈጸመ ይገኛል።

አሸባሪው ህወሓት ንጹሃን ዜጎችን በጅምላ እየጨፈጨፈ፣ እያፈናቀል፣ የሐይማኖት ተቋማትን ጨምሮ የመሰረተ ልማቶች እያፈራረሰ፣ የቻለውን ሀብት ንብረት እየዘረፈ፣ ያልቻለውን እያወደመ የሕዝቡን  ሰላም እያወከ መሆኑን  ተናግረዋል።

ዋና አስተዳዳሪው እንዳሉት አሸባሪው ህወሓት የደቀነውን ወቅታዊ የሕልውና አደጋ ለመቀልበስ መንግስት እየወሰደ ያለውን እርምጃ በበመደገፍ ዞን ህዝብ ልጆቹን ወደግንባር በመላክና ሁሉን አቀፍ ድጋፍ በማድረግ አለኝታነቱን እያሳየ ነው።

አሸባሪው ህወሓት ሀገር ዘርፎ ባከማቸው ሀብት በውስጥና በውጭ በሚነዛው የሀሰት ፕሮፖጋንዳ ዘመቻ ሸብረክ ሳንል ለሀገራችን አንድነት በፅናት ዘብ መቆማ አለብን ብለዋል።

ከተባበርንና አንድነታችንን ጠብቀን ከዘለቅን የማናሸንፈው ምድራዊ ኃይል እንደመይኖር የአድዋና የካራማራ የድል ታሪካችን ህያው ምስክሮች መሆናቸው በአብነት አመላክተዋል።

የዞኑ ህዝብ ቀደም ሲል  ለሕልውና ዘመቻው ከ40 ሚሊዮን ብር በላይ በአይነትና በጥሬ ከንዘብ ድጋፍ ያደረገ ሲሆን  በዛሬው ዕለት 10 ሚሊዮን 162 ሺህ ብር የሚገመት የ248 ሰንጋ በሬዎች፣ የበግና የፍየል ሙክቶች ድጋፍ ማበርከቱን አስታውቀዋል።

ከሕዝባዊ ሰልፉ ተሳታፊዎች መካከል ወይዘሮ አለሚቱ ደምሴ እንዳሉት ሁለት ወንድና ሴት ልጆቻቸውን የሀገር መከላከያ ሠራዊትን እንዲቀላቀሉ መርቀው ሸኝተዋል።

"እኔም ብሆን ከልጆቼ ጎን ተሰልፌ ለመዋደቅ ዝግጁ ነኝ" ያሉት ወይዘሮ አለሚቱ ከሀገር ሠላም የሚበልጥ ስለማይኖር ዕድሜና ፆታ ሳይለይ ሁሉም ለሕልውና ዘመቻው በአንድነት መነሳት አለበት ብለዋል።

 አቶ ሙስጠፋ ረዲ እንዳሉት ኢትዮጵያ በአሁኑ የውጭም የውስጥም ጠላቶቿ የተነሱበት ወቅት በመሆኑ ሁላችንም ከመንግሥትና ከሀገር መከላከያ ጎን በመቆም አለኝታነታችን ማሳየት ይገባናል፡፡

እስካሁን ከወር ደመወዛቸው ቀንስው በመስጥ ጭምር ለሀገር መከላከያ ሠራዊት ድጋፍ በማድረግ ለሠራዊቱ አጋርነታቸውን ማሳየታቸውን ገልጸዋል።

አሸባሪው ህወሓት ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ለማጥፋትና የውጭ ኃይሎችን ሴራ ለማምከን የሚጠበቅባቸው ሁሉ ለማድረግ ዝግጁ መሆናቸውን ገልጸዋል።

ወጣት ሬድዋን ከይረዲን በበኩሉ በሀገራችን ላይ የተጋረጠውን ወቅታዊ የሕልውና አደጋ ለመቀልበስ እንደ አባቶቻችን አንድነታችንን መጠበቅና ተባብረን መነሳት አለብን ብሏል።

ኢትዮጵያን እድገቷን በማይመኙ የውስጥ ባንዳዎች ጭምር ከተደቀነባትን ወቅታዊ የሕልውና  አደጋ ለመታደግ እስከ ግንባር ድረስ በመዝመት የሕይወት መስዋዕትነት ለመክፈል መዘጋጀቱንም ተንግሯል።

ሕዝባዊ የድጋፍ ሰልፉ ወራቤን ጨማሮ በዞኑ አምስት ማዕከላት የተካሄደ ሲሆን ለሀገር መከላከያ ሠራዊት  የደም ልገሳ መርሀ-ግብርም ተከናውኗል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም