"ልጆች ከሀገር ክብርና ሉአላዊነት አይበልጡም "---በዲላ ልጆቻቸውን መርቀው የላኩ እናቶች - ኢዜአ አማርኛ
"ልጆች ከሀገር ክብርና ሉአላዊነት አይበልጡም "---በዲላ ልጆቻቸውን መርቀው የላኩ እናቶች
ዲላ ጥቅምት 28/2014 "ልጆች ከሀገር ክብርና ሉአላዊነት አይበልጡም ፤ ሁሉም የሚሆነው ሀገር ሲኖር ነው" ይላሉ ከሁለት በላይ ልጆቻቸውን መከላከያ ሠራዊቱን እንዲቀላቀሉ መርቀው የላኩ የዲላ እናቶች።
ኢትዮጵያን ለማፍረስ አልሞ የተነሳው አሸባሪው ህወሓት በመከላከያ ሠራዊት የሰሜን እዝ ላይ የፈጸመው ጥቃት ሳይበቃ በወረራ በያዛቸው አካባቢዎች ንጹንን ለሞት፣ ለስቃይና ለመፈናቀል ዳርጓል።
ቡድኑ በየደረሰበት ህጻናትና ሴቶችን ጨምሮ በዜጎች ላይ ከፈጸመው ዘግናኝ ግፍ ባላፈ የሀገርና የህዝብ ሀብት በመዝረፍና በማውደም ጥርስ የነቀለበትን የውንብድና ተግባር ዛሬም ቀጥሎበታል።
አሸባሪው ህወሓት በሀገርና በህዝብ ላይ እየፈጸመ ያለውን ግፍና በደል ለማስቆምና ግብአተ መሬቱን በተባበረ ክንድ ለመፈጸም ኢትዮጵያውያን ሆ ብለው ተነስተዋል።
መከላከያ ሠራዊትና ሌሎች የጸጥታ አካላት በተለያየ ግንባር የጥፋት ቡድኑን አከርካሪ ለመስበር እያደርጉት ላለው ትንቅንቅ ኢትዮጵያውያን በተለያየ መንገድ ደጀንነታቸውን አሳይተዋል።
ለእዚህም በየአካባቢው እናቶች ከስንቅ ዝግጅት ጀምሮ አምጠው ለወለዷቸው ልጆች ሳይሰስቱና ሀገርን በማስቀደም ወደጦር ግንባር መርቀው ልከዋል፤ በእዚህም ታሪካዊ አሻራቸውን አሳርፈዋል።
ሁለትና ከሁለት በላይ ልጆቻቸውን ለሀገር ክብርና ሉአላዊነት ሲሉ ወደጦር ግንባር የላኩ የዴላ ከተማ እናቶች ደግሞ በእዚህ ደማቅ የኢትዮጵያውያን ታሪክ ውስጥ ሌላ አዲስ ምዕራፍ ከፍተዋል።
እናቶቹ ጧሪና ተንከባካቢ ቢያስፈልጋቸውም "ሁሉም የሚሆነው ሀገር ሲኖር ነው" በሚል ተነሳስተው ልጆቻቸውን መርቀው ወደጦር ግንባር ልከዋል።
ወደትግል የላኳቸው ልጆች በድል እስኪመለሱ ድረስ አካባቢያቸውን በንቃት በመጠበቅ የበኩላቸውን እንደሚወጡም ነው እናቶቹ የገለጹት።
ኢዜአ ካነጋገራቸው እነዚህ እናቶች መካከል ወይዘሮ መሰረት ባሻ እንዳሉት የውስጥና የውጭ ሃይሎች ተቀናጅተው ጫና በመፍጠር ኢትዮጵያን ለማፍረስ የያዙት ውጥን ከዳር አይደርስም።
ከዚህ ቀደም እብሪተኛው ዚአድባሬ ኢትዮጵያን በወረረበት ወቅት የዘመቱ ሁለት ወንድሞቻቸውን ጨምሮ የኢትዮጵያ የቁርጥ ቀን ልጆች በከፈሉት መስዋዕትነት የሀገር ክብርንና ሉአላዊነት ተጠብቆ መቆየቱን አስታውሰዋል።
ዛሬም አሸባሪው ህወሓት በእብሪት ተነሳስቶ ሀገር ለማፍረስ እየፈጸመ ያለው የጥፋት ተግባር ያንገበገባቸው ወይዘሮ መሰረት፣ ሁለት ልጆቻቸውን ወደግንባር ልከዋል።
"ሀገር ከምንም በላይ ነው" የሚሉት እኚህ እናት፣ አንድ ሴትና አንድ ወንድ ልጆቻቸው መከላከያ ሠራዊቱን እንዲቀላቀሉ መርቀው መሸኘተቸውን ይናገራሉ።
ወይዘሮ መሰረት እንዳሉት በየአካባቢው የወጣቱና የሚኒሻው መነሳሳት ለሀገር ክብርና ለዜጎች ደህንነት መስዋዕትነት ለመክፈል ያላቸውን ቁርጠኝነት የሚያሳይ ነው።
"መርቄ የላኳቸው ልጆቼ በድል እስኪመለሱ ድረስ አካባቢያችንን በንቃት ከመጠበቅ ባለፈ የአሸባሪውን ተላላኪዎችና ሰርጎ ገቦችን አጋልጦ ለህግ አካላት በመስጠት የበኩሌን እወጣለሁ" ብለዋል።
"ብዙ ለፍቼ ያለአባት ያሳደኳቸውን ሁለት ልጆች ከሀገር ክብርና ሉአላዊነት አይበልጡም በሚል ሠራዊቱን እንዲቀላቀሉ መርቄ ልኬያቸዋለው" የሚሉት ደግሞ ወይዘሮ አስናቀች ዳምጠው ናቸው።
"በማረፊያዬ ወቅት ልጆቼ ከአጠገቤ መራቃቸው ቢጎዳኝም ሁሌም ደስተኛ መሆን የሚቻለው ሀገር ስትኖር በመሆኑ ኢትዮጵያን ለማቆየት ልጆቼ ዘምተዋል" ብለዋል።
የዕድሜና የአቅም ጉዳይ ሆነ እንጂ እሳቸውም ቢሆኑ ከልጆቻቸው ጋር በመዝመት ጠላትን በግንባር ቢፋለሙ ምርጫቸው መሆኑን ነው የገለጹት።
ከዚህ ቀደም ሁለት ልጆቻቸውን፤ በህልውና ዘመቻው ደግሞ ተጨማሪ ሁለት በአጠቃላይ 4 ልጆቻቸውን መርቀው መላካቸውን የገለጹት ደግሞ ወይዘሮ መድሃኒት ግርማ ናቸው።
ሀገር እንድትቀጥል የልጆቻቸው መስዋዕትነት አስፈላጊ በመሆኑ ምንም ቅሬታ እንዳልገባቸው የገለጹት እኚህ እናት፣ "ልጆቼ ጠላትን አሳፍረው በድል ይመለሳሉ" ሲሉ ተስፋቸውን ተናግረዋል።
የዲላ ከተማ ከንቲባ አቶ ተስፋጽዮን ዳካ በበኩላቸው፣ "ሀገር ለማዳን ከሁለት በላይ ልጆቻቸውን የላኩ እናቶች ለእኛም አርአያ ይሆናሉ" ብለዋል።
የከተማው አስተዳደር ልጆቻቸው በመዝመታቸው ምክንያት በእናቶች ኑሮ ላይ ክፍተት እንዳይፈጠር ከተማ አስተዳደሩ አስፈላጊውን ድጋፍ ሁሉ እንደሚያደርግ አረጋግጠዋል።