ቀጥታ፡

ኢትዮጵያን ለማዳንና ህልውናዋን ለማረጋገጥ መስዋእትነት እንከፍላለን -የሐረሪ ክልል ነዋሪዎች

ሐረር ጥቅምት 28 ቀን 2014 (ኢዜአ) ከጀግናው መከላከያ ሠራዊት ጎን በመሰለፍ ኢትዮጵያን ለማዳንና ህልውናዋን ለማረጋገጥ መስዋእትነት እንከፍላለን ሲሉ የሐረሪ ክልል ነዋሪዎች ገለጹ።
በክልሉ ሀገር ከተማ ጨምሮ ከገጠር ቀበሌ የተውጣጡ ነዋሪዎች፣ የጸጥታ አካላት፣ተማሪዎች፣አርሶ አደሮች ናሌሎች የማህበረሰብ ክፍሎች አሸባሪዎቹን ህወሀትና ሸኔን በማውገዝና መከላከያ ሰራዊትን  በመደገፍ ዛሬ በሀረር ከተማ ታላቅ ህዝባዊ ሰልፍ አካሂደዋል።

ከጀግናው መከላከያ ሠራዊት ጎን በመሰለፍ ከሽብርተኞች ህወሃትና ሸኔ ሴራ ሀገርን ለማዳን ሁለንተናዊ ድጋፍ እንደሚያደርጉ  ነዋሪዎች አስታውቀዋል።

ነዋሪዎቹ አሜሪካንና ምዕራብያውያን የአገሪቱን እውነታ ወደ ጎን በመተው ኢትዮጵያ ላይ  ጫና ለመፍጠር እያደረጉ ያለውን  ጣልቃ ገብነት አውግዘዋል ።

ከነዋሪዎቹ መካከል ወይዘሮ ኢፍቱ ተስፋዬ ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ  "ሁሉም ነገሬ ሀገሬ ናት፤ በአሁኑ ወቅት ሀገሬን ከመፍረስ አደጋ ለመታደግ መስዋትነት ለመክፈል ዝግጁ ነኝ" ብለዋል።

አሸባሪዎቹ ህወሀትና ሸኔን ለመደምሰስና ግብዓተ መሬት ለማስገባት እየተካሄደ ባለው የህልውና ዘመቻ ከመከላከያ ሰራዊት ጎን ለመቆም ዝግጁ  መሆናቸውን ተናግረዋል።

"ወጣት ሄኖክ በቀለ በበኩሉ ሀገር የማዳን ጉዳይ በእያንዳንዳችን ትከሻ ላይ ያረፈ ወቅታዊ ኃላፊነት በመሆኑ በዕውቀቴ የጠራ መረጃ ለህዝብ በማቀበል፣ በገንዘብና ግንባር በመዝመት ሀገሬን ለማዳን ተዘጋጅቻለሁ" ብሏል።

ሌላው ወጣት ቴዎድሮስ ንጉሴ በበኩሉ "ከሽብርተኞቹ ህወሃትና ተላላኪዎቹ ጥቃት ሀገርን ለማዳን እንደ ወጣትነቴ ከሠራዊቱ ጎን በመቆም ለመዋጋት ቆርጫለው" ብሏል።

አሜሪካና አንዳንድ አውሮፓ ሀገራት መንግስታትና  መገናኛ ብዙሀኖቻቸው በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ ከመግባት መታቀብ አለባቸው፤ በውስጥም ሆነ በውጭ የምንኖር ኢትዮጵያዊያን ድምፃችንን ማሰማት ይኖርብናል" ሲሉ ነዋሪዎቹ አመልክተዋል።

የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኦርዲን በድሪ በሰልፉ ላይ እንደተናገሩት አሸባሪው ህወሓት በስልጣን ቆይታው 27 አመታት የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦችን ሲጨቁንና ሲዘርፍ ቆይቷል።

"አሸባሪው  በአሁኑ ወቅት እየተፍጨረጨረ ያለው ሀገር የመፍረስ ተግባር አይሳካም" ብለዋል።

"ሀገር ለማፍረስ የተነሱ ህወሀትና ሌሎች አሸባሪዎችን መታገል ይገባል" ያሉት ርዕሰ መስተዳደሩ ኢትዮጵያ አትፈርስም፤ በልጆቿ ጥረት ታፍራና ተከብራ ትኖራለች" ሲሉ መልእክት አስተላልፈዋል።

የክልሉ ህዝብ የህይወት መስዋትነት በመክፈል ሀገርን እየታደጉ የሚገኙ የመከላከያ ሰራዊትና የክልል የፀጥታ አካላትን በመደገፍ እንዲሁም በግንባር ዘመቻውን በመቀላቀል  ተሳትፎውን አጠናክሮ እንዲቀጥል አስገንዝበዋል።

"ሀገራችን ከመቼውም ጊዜ በላይ የምትፈልገን ወቅት ላይ ነን" ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ የክልሉ ነዋሪ አካባቢውን በንቃት በመጠበቅና ፀጉረ-ልውጦችን በጋለጥ እንዲሁም  ከፀጥታ አካላት ጋር በቅንጅት መስራት ይገባዋል" ሲሉ  አስገንዝበዋል።

"በከሀዲዎች መቃብር ላይ የኢትዮጵያን ብልፅግና እናረጋግጣለን፤ ለዚህም በተባበረ ክንድ በአንድነት መቆም ይገባል" ብለዋል።

ህብረተሰቡ ከመቼውም ጊዜ በላይ የመረዳዳት ባህሉን በማጠናከር በጦርነቱ ምክንያት የተፈናቀሉ ዜጎችን እንዲደግፍ ርዕሰ መስተዳደሩ ጥሪ አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም