ኢትዮጵያዊነትን በማስቀደም ለሰራዊታችን ድጋፍ እናደርጋለን - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያዊነትን በማስቀደም ለሰራዊታችን ድጋፍ እናደርጋለን
ጥቅምት 28 ቀን 2014 (ኢዜአ) ኢትዮጵያዊነትን በማስቀደም ለአገር መከላከያ ሰራዊት ሁሉን አቀፍ ድጋፍ እንደሚያደርጉ በመስቀል አደባባይ ሰራዊቱን ለመደገፍና አሸባሪዎቹን ሸኔና ህወሃት ለማውገዝ በተካሄደው ሰልፍ ላይ የተሳተፉ ሴቶች ተናገሩ፡፡
ሰልፉ ላይ የተገኙ ሴቶች ሃገራችንን አሳልፈን አንሰጥም፣ኢትዮጵያ ወደፊት እንጂ ወደ ኋላ አትመለስም ሲሉ ተደምጠዋል፤ ለዚህም የሚጠበቅባቸውን የዜግነት ግዴታ እንደሚወጡ ነው የተናገሩት ፡፡
በሰልፉ በመሳተፍ ድምጻቸውን ያሰሙት አሸባሪው ህወሃት ሃገራችን ወደ ብልፅግናን የምታደርገውን ጉዞ ለማደናቀፍ የሚፈጽመውን ሴራ ዓለም እንዲያውቀው በማሰብ እንደሆነ ተናግረዋል።
አሸባሪው ቡድን በሃሰት ፕሮፓጋንዳ ዳግም የኢትዮጵያ ህዝብ ጫንቃ ላይ መውጣት እንደማይችል ገልጸዋል።ቡድኑ ሲፈጽማቸው በነበሩ ተግባሮች በህዝብ ዘንድ እንደተጠላም ገልጸዋል።
ኢዜአ ያነጋገራቸው እንስት የሰልፉ ተሳታፊዎች ለአገር መከላከያ ሰራዊት የሚያደርጉትን ድጋፍ እንደሚያጠናክሩ ጠቁመዋል።ከዚህ ቀደም የገንዘብና የስንቅ ድጋፍ ማድረጋቸውን አስታውሰዋል።
የውጪ ጣልቃ ገብነትን አውግዘው በሚመራን መንግስት እናምንበታለን ሲሉ አስረግጠዋል ፡፡ሰራዊቱን በጉልበትና በገንዝብ ለመደገፍ ካላቸው ቀንሰው አስተዋጽኦ እንደሚያደርጉ ተናግረዋል።
በሰፈር በሚደረጉ ጥሪዎች በደስተኝነት እንደሚሳተፉ ገልፀው፤ “በሃገር ጉዳይ አንደራደርም፣ አገራችንን አሳልፈን አንሰጥም፣ አገር የሚሸጡ ሌቦችን እና ባንዳዎችን አሳልፈን መስጠት አለብን” ብለዋል፡፡
ሴቶቹ እስከ ግንባር ለመዝመት ቁርጠኝነቱ እንዳላቸውና የውስጥ ባንዳዎችን በማጋለጥ እንደሚሰሩ ገልፀው፤ “አባቶች ያስረከቡንን ሃገር ለትውልዱም ያልተከፋፈለች ኢትዮጵያን ለማሻገር እንስራ” ብለዋል፡፡
እኛ ኢትዮጵያውያን “የምንሰደድበት ሀገር የለንም “ ያሉት ለድጋፍ የወጡ ሴቶች አንድነትን ለመፍጠር እንስራ ሲሉ መልእክት አስተላልፈዋል ፡፡