ቀጥታ፡

የሕልውና ዘመቻው ዋነኛ ግብ አሸባሪው ህወሓት ዳግም የኢትዮጵያ ስጋት እንዳይሆን መደምሰስ ነው

እንጅባራ (ኢዜአ) ጥቅምት 28/2014 የሕልውና ዘመቻው ዋነኛ ግብ አሸባሪውን ህወሓት ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ በመደምሰስ ዳግም የኢትዮጵያ ስጋት እንዳይሆን ማድረግ ነው ሲሉ የአዊ ብሔረሰብ አስተዳደር ዞን ዋና አስተዳዳሪ ገለጹ።

የክተት  ጥሪውን ተቀብለው በሕልውና ዘመቻው ለመዝመት የተዘጋጁ ኢትዮጵያውያን እንዳሉት የአሸባሪ ህወሓትን ግብዓተ መሬት ለመፈጸም ቆርጠው ተነስተዋል።

በዞኑ የክተት ጥሪ ተቀብለው ከአሸባሪ ህወሓት ጋር ለመፋለም የተዘጋጁ ሚሊሻዎች፣ የቀድሞው ሠራዊት አባላትና የጤና ባለሙያዎች ወደ ግንባር ተሸኝተዋል።

የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ አቶ እንግዳ ዳኛው በሽኝት ስነ ስርዓቱ ላይ እንዳሉት ዘመቻው በወረራ የተያዙ አካባቢዎችን ከህወሓት ማስለቀቅ ያለፈ ግብ አለው።

የአሸባሪ ህወሓትን ግብዓተ መሬት በመፈጸም ለኢትዮጵያ ዳግም ስጋት እንዳይሆን ማድረግ ዋነኛ ጉዳይ በመሆኑ የዞኑ ዘማቾች ለሕልውና ዘመቻው ስኬት በጋራ ርብርብ ያደርጋሉ።  

በሕልውና ዘመቻው አሸባሪው ህወሓትን በአጭር ጊዜ ውስጥ ለማጥፋት ኢትዮጵያውያን ሁሉን አቀፍ ትግል እያደረጉ መሆኑን አመልክተዋል።

ዋና አስተዳዳሪው እንዳሉት ዘማቾች ሀገር ለማዳን ያሳዩት መነሳሳት ጀግኖች አባቶቻችን ኢትዮጵያን ለማቆየት የከፈሉትን የመስዋዕትነት ታሪክ ትውልዱ በተግባር ማስቀጠሉን ያሳያል።  

"የክተት ዘመቻው ለነፃነትና ሀገር ለማስቀጠል የሚደረግ በመሆኑ እያንዳንዳችን ልንዘምት ይገባል።"ያሉት አስተዳዳሪው ኅብረተሰቡ የዘማች ቤተሰቦችን በመንከባከብና በመደገፍ ደጀንነቱን አጠናክሮ እንዲቀጥል አሳስበዋል።

ከዘማቾቹ መካከል ሚሊሻ ጥላዬ ተገኘ "ወራሪው ከኢትዮጵያ ምድር እስኪጠፋ ድረስ በመፋለም ልጆቼ የሚኮሩበት ታሪክ እሰራለሁ።" ብለዋል።

"አሸባሪው ህወሓት በማናለብኝነት ሲፈነጭ እንደማየት የሞት ሞት የለም ያሉት ሚሊሻው፤ ሙሉ በሙሉ ተደምስሶ የወገን ሞትና ስቃይ እስኪቆም ድረስ እፋለመዋለሁ።" ሲሉም አረጋግጠዋል።

በሚሰማሩበት ግንባር ከመከላከያ ጋር በመሆን አሸባሪውን ቡድን በመደምሰስ  የወረራቸውን አካባቢዎች ነፃ እንደሚያወጡም ተናግረዋል።

የጤና ባለሙያው ደሳለኝ ሙለዓለም በተሰማሩበት የጤና መኮንንነት ለማገልገል የሕልውና ዘመቻውን መቀላቀላቸውን ተናግረዋል።

ጀግናው የወገን ጦር የህወሓትን ግብዓተ-መሬት ለማረጋገጥ ሲፋለም ለሚደርስበት ድንገተኛ ጉዳት የህክምና አገልግሎት በመስጠት ሃላፊነቴን እወጣለሁ ብለዋል።

"በአሁኑ ወቅት ከሠራዊቱ ጋር የማይሰለፍ ሙያተኛ ሊኖር አይገባም" ያሉት አቶ ደሳለኝ፣ ለትግሉ አስተዋጾ ያላቸው ሙያተኞችም ሠራዊቱን እንዲቀላቀሉ ጥሪ አቅርበዋል።

"ወራሪው በደረሰባቸው አካባቢዎች የፈጸመውንና እየፈጸመ ያለውን ዘግናኝ ግፍ እየሰማን ሥራ መስራት አይቻልም" ያሉት ደግሞ  የመንግስት ሠራተኛ ዘማች አቶ ደርበው በላይ  ናቸው።

ጠላትን ለመፋለም እየተመመ ካለው ህዝባዊ ማዕበል ጋር በመሆን አሸባሪውን ለመደምሰስ በቁርጠኝነት መነሳታቸውን ገልጸዋል።

"በእዚህም ሀገራዊ አደራን በመወጣት የአባቶቻችን ገድል መድገም እፈልጋለሁ" ብለዋል።

ዘማቾቹ አሸባሪው ህውሓትን በመደምሰስ የሀገርና የህዝብ ደሀንነትን ሳያረጋግጡ ወደቄያቸው እንደማይመለሱም አረጋግጠዋል።

በክተት ጥሪው ከዞኑ ሁሉም ወረዳዎች የተሰባሰቡ በየደረጃው ያሉ አመራሮች፣ የሕክምና ባለሙያዎችን ጨምሮ የመንግሥት ሠራተኞች፣ የቀድሞ ሠራዊትና የሚሊሻ አባላት ሀገር ለማዳን የሕልውና ዘመቻውን ተቀላቅለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም