ቀጥታ፡

የጥናት ሪፖርቱ ኢትዮጵያን ለማፍረስ ሲሰሩ ለነበሩ ሁሉ እውነታውን ያጋለጠ ነው ---የህግ ምሁራን

ሚዛን አማን ጥቅምት 28/2014(ኢዜአ) የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብዓዊ መብት ቢሮና የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን በጋራ ያቀረቡት የጥናት ሪፖርት በሀሰት መረጃ ኢትዮጵያን ለማፍረስ ሲሰሩ ለነበሩ ሁሉ እውነታውን ያጋለጠ ነው ሲሉ ምሁራን አስታወቁ።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ያነጋገራቸው የሚዛን አማን ዩኒቨርሲቲ የህግ ምሁራንና ባለሙያዎች እውነት ተቀብራ እንደማትቀር ገልጸው ኢትዮጵያን ለማፍረስ የተነሳውን ህወሓት አከርካሪ ለመስበር ሪፖርቱ አስተዋጾ እንደሚኖረው ተናግረዋል።

በሚዛን ቴፒ ዩኒቨርሲቲ የህግ ትምህርት ክፍል መምህር አዳነ ኮረቦ እንዳሉት መንግስት እንዳጠፋ አድርገው እየወነጀሉ ሲዘግቡ የቆዩ የውጭ መገናኛ ብዙሀን የህወሓት ወገንተኛ መሆናቸው በግልጽ ታይቷል።

"የጥናት ሪፖርቱ የማይካድራ ጭፍጨፋ በህወሓት እንደተፈጸመ ይፋ ማድረጉ ለኢትዮጵያ እውነታ አንድ ማስረጃ ነው" ብለዋል።

ድርጊቱ በመንግስት እንደተፈጸመ ሀሰተኛ ወሬ ሲነዙና ለጉዳዩ ትኩረት ላልሰጡት የውጭ መገናኛ ብዙሀን ለአሸባሪው ህወሀት ያላቸውን ወገንተኝነት ያመላከተ መሆኑን ጠቅሰዋል።

መምህር አዳነ እንዳሉት አሸባሪው ህወሓት የፈጸመው ጭፍጨፋ ለዓለም እንዳይጋለጥ በአፈ ቀላጤ ተላላኪዎቹ በኩል ሲሰራ ቢቆይም ሀገር አፍራሽ መሆኑ በሪፖርቱ ተጋልጧል።

መንግስት ህወሓትን በአሸባሪነት የፈረጀበት ምክንያት አሳማኝ ስለመሆኑ አንድ ማሳያ እንደሆነም ነው የገለጹት

"ሪፖርቱ ኢትዮጵያ ህልውናዋን ለማስጠበቅ፤ አሸባሪው ደግሞ የሽብር ተግባሩን በንጹሃንና በሀገር ላይ ለመፈጸም ሲንቀሳቀስ እንደነበር ግንዛቤ የሚያስጨብጥ ነው" ብለዋል።

እንደ መምህሩ ገለጻ ሪፖርቱ ከትግራይ ክልል ውጪ በአሸባሪው የተፈጸሙ የሰብአዊ መብት ጥሰቶችን ያካተተ ቢሆን ኖሮ ከዚህም የበለጠ የቡድኑን አረመኔያዊነት በአደባባይ ይጋለጥ ነበር።

አሸባሪው በወረራ በያዛቸው አካባቢዎች ያለጥፋታቸው በግፍ ጭካኔ በተሞላበት መንገድ የጨፈጨፋቸውን ንጹሀን ለማጋለጥ ይቻል እንደነበር አመልክተዋል።   

"የተፈጸሙ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን ለማወቅ የሚካሄዱ ጥናቶች በቀጣይም ተጠናክረው መቀጠል ይኖርባቸዋል" ሲሉም መምህር አዳነ ተናግረዋል።

ሌላው የህግ ባለሙያ ተሾመ ናካ በበኩላቸው "አሸባሪው ህወሓት  በዓለም ዓቀፉ የሰብዓዊ መብት ድንጋጌዎች የተቀመጡ ህጎችን መጣሱን ሪፖርቱ ይፋ አድርጓል" ብለዋል።

ሪፖርቱን መነሻ አድርገው እንደገለጹት አሸባሪው ቡድን በዓለም አቀፍ ህግ የተከለከሉ ህጻናትን ለጦርነት ማሰለፍ፣ ሰላማዊ ሰዎችን በከባድ መሳሪያ ጭምር መምታት፣ ሴቶችን መድፈርና መሰል ድርጊቶችን ፈዕሟል።

ይሁንና አሸባሪው ቡድን ድርጊቱን የኢትዮጵያ መንግስት የፈጸመው አድርጎ በማቅረብ የዓለም ህዝብ የተሳሳተ እይታ እንዲኖረው አድርጓል።

በዚህም ዓለማቀፉ ማህበረሰብ በተለይ ምዕራባዊያን ኢትዮጵያ ላይ የተለያዩ ማዕቀቦች እንዲጣሉ በግልጽ ሲሰሩ መቆየታቸውን ጠቅሰዋል።

የሰበአዊ መብት ኮሚሽኖቹ ሰሞኑን ይፋ ያደረጉት ሪፖርት በተቃራኒው አሸባሪው ቡድን የጭካኔ ድርጊቶቹን ራሱ የፈጸመው ወንጀል እንደሆነ ማሳየቱ ለኢትዮጵያ ትልቅ ድል፤ ለቡድኑ ደግሞ ሽንፈት መሆኑን ገልጸዋል።

የህግ ባለሙያው እንዳሉት ሪፖርቱ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ የህወሓትን አሸባሪነት አምኖ እንዲቀበል የሚያስችል መረጃ የሰጠ ነው።

አቶ ተስፋዬ ሽመልስ የተባሉ ሌላው የህግ ባለሙያ በበኩላቸው ኢትዮጵያ ትክክለኛነትና እውነት ቢኖራትም ምዕራባውያኑ ማወቅ ባለመፈለጋቸው ምክንያት ጉዳዩ ተሸፋፍኖ መቆየቱን አስረድተዋል።

የጥናት ሪፖርቱ የኢትዮጵያ መንግስትና መከላከያ ሠራዊቱ በኃላፊነት የሚንቀሳቀሱ መሆኑን ያረጋገጠ መሆኑን አመልክተዋል።

እንደ ባለሙያው ገለጻ ኢትዮጵያን እንዳሻቸው ማዘዝ የሚሹ አካላት ዓላማቸውን ለማሳካት ዛሬም በመገናኛ ብዘሀኖቻቸው የተቀናጀ፣ ሀሰተኛና ለአንድ ወገን ያደላ ዘመቻቸውን ቀጥለውበታል።

"ሰሞኑን ይፋ የተደረገው ሪፖርት መገናኛ ብዙሀኑ የሚያሰራጩት መረጃ ሀስት መሆኑን የኢትዮጵያ ህዝብ እንዲያውቅ ከማድረጉ ባለፈ የህወሓት ዓላማ እንዳይሳካ ያዝጋል" ብለዋል።

መገናኛ ብዙሀኑ በገለልተኛ አካል የተጠናውና ይፋ የተደረገውን ውጤት አድበስብሰው በዝምታ ማለፋቸው የበለጠ ትዝብት ውስጥ እንደሚከታቸው ተናግረዋል።

"ይፋ የተደረገው ሪፖርት የህልውና ዘመቻው ሲጠናቀቅ በዓለም ዓቀፍ ህግ ተጠያቂ የሚያደርጉ ከባድ ወንጀሎች እንደተፈጸሙ ያሳየ ነው" ሲሉም የህግ ባለሙያው አክለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም