"ለኢትዮጵያ ነጻነትና ክብር የምንሰስተው ሕይወት የለም" - ኢዜአ አማርኛ
"ለኢትዮጵያ ነጻነትና ክብር የምንሰስተው ሕይወት የለም"
ጥቅምት 28/2014 (ኢዜአ )"ለኢትዮጵያ ነጻነትና ክብር የምንሰስተው ሕይወት የለም" ሲሉ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ ተናገሩ።
አሸባሪዎቹን ሕወሓትና ሸኔ እንዲሁም በኢትዮጵያ ላይ ግልጽ ጫና እያሳደጉ ያሉ የውጭ ሃይሎችን የሚያወግዝ ህዝባዊ ሰልፍ በአዲስ አበባ ተካሄዷል።
በሰልፉ ላይ የተገኙት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ "አገር አንድ ናት መለወጫ የላትም አገር ሰላም ከሌላት እኛ ሰላም የለንም አገር ከተደፈረች ሕዝቦቿ ይደፈራሉ፤ የአገር ሉላዓዊነት ቀይ መስመሩ ከታለፈ ነጻነት የለም ፍትሐዊነት የለም ክብር የለም " ሲሉ መልእክታቸውን አስተላልፈዋል።
የአሁኑ ትውልድ የኢትዮጵያን ነጻነት ክብር አንድነትና አብሮነት ለማስከበር ቆራጥ መሆኑን አመልክተዋል።
ከሶስት ዓመት በፊት ኢ-ፍትሐዊነትና ጭቆና አንቀብልም አገር መከፋፋል ሴራ ይቁም፤ ኢትዮጵያን እንለውጥ ፍትሐዊ ተጠቃሚነት ይስፈን በሚል የኢትዮጵያ ወጣቶች ባደረጉትን ትግልና በከፈሉት መስዋዕትነት ነጻነት አግኝተናል ብለዋል።
ሆኖም ያገኘነውን ነጻነት ሊነጥቀን የሚፈልግ ማንኛውም ሃይል የምንታገስበት ትከሻ የለንም ነው ያሉት ከንቲባዋ "የአድዋ ልጆች መሆናችንን ረስተው በአጎዋ ሊያስፈራሩን የሚሞክሩት፤ አድዋ ነፃነት፤ አጎዋ ደግሞ እርዳታ መሆኑ ስላልገባቸው ነው" ብለዋል።
"አሸባሪውና ጁንታው ቡድን ትናንት ያደረገው ጥፋት ሳያንሰው አዲስ ምዕራፍ በጀመርነበት ማግስት ላይ ጦርነት ከፍቶብናል" ያሉት ከንቲባዋ "የሸኔ ተላላኪዎች እነሱ የሚጋልቧቸውና ሌሎች መሰለሎች ይሄንኑ ለማስፈጸም ተነስተዋል" ብለዋል።
አሸባሪው ህወሃት ኢትዮጵያን ለማፍረስ ሲኦልም ቢሆን እገባለሁ ማለቱን አስታውሰው "የሕወሓት ቡድን ትክክለኛ መኖሪያውና ስፍራው ሲኦል መሆኑን ስለሚያውቅ ነው" ሲሉ ገልጸዋል።
ኢትዮጵያዊያን ዴሞክራሲያዊ መብታቸውን ተጠቅመው የመረጡን መንግስት "እኛ ያልነው መንግስት ካልሆነ እንቀብልም የአሻንጉሊት መንግስት እናስቀምጥላችሁ" ብለው ምኞታቸውን ማሳያታቸውን ተናግረዋል።
መገናኛ ብዙሃንም በማዝመት ላለፉው አንድ ዓመት የኢትዮጵያን ስም ለማጠልሸትና ዓለም እንዲያድምብን በተቀናጀ መልኩ ውሸትን እየዘገቡ እንደሚገኝ አመልክተዋል።
ሕዝባችንን በተለይም የአዲስ አበባን ሕዝብ ለማሸበር አዲስ አበባ ተከባላች እያሉ እየዘገቡ ነው ያሉት ከንቲባዋ "አዲስ አባበ የተከበበችው በሚጠብቋት ድንቅ ልጆቿ ነው" ብለዋል።
በነጻታችንና ኢትዮጵያ ከመጡብን የምንሰስተው ሕይወት የለም፤ የምንሰስተው ጊዜ ጉልበትና ንብረት የለም ብለዋል ከንቲባዋ።
ለኢትዮጵያ አንድነትና ክብር እንደ አንድ ልብ መካሪ እንደ አንድ ቃል ተናጋሪ መሆናችንን በተግባር አሳይተናልም ነው ያሉት።
"በባርነት አልኖርንም ባርነትን አልወረስንም፤ በባርነትም እንኖርም" በማለት ለኢትዮጵያ ሉዓላዊነትና ክብር ለሚዋደቁ የአገር መከላከያ ሰራዊት አባላት ጎን በመቆም መደገፍ እንደሚገባ ገልጸዋል።
ኢትዮጵያን ለማዳን መዝመት አለብን፤ በገንዝብና በሀብትም መደገፍ አለብን ያሉት ከንቲባዋ መላ የአዲስ አበባ ነዋሪ የከተማዋን ሰላም በዘላቂነት እንዲያስጠብቅም አሳስበዋል።