ጣልቃ ገብነትን የመመከቻ ሰዓቱ አሁን ነው - ኢዜአ አማርኛ
ጣልቃ ገብነትን የመመከቻ ሰዓቱ አሁን ነው
ከቀዝቃዛው ጦርነት ማግስት ጀምሮ ዓለም የተሻለ ገጽታ ይኖራታል የሚል እምነት በብዙዎች ዘንድ ነበር። የሁለቱ ሃያላን ፍጥጫ በአንደኛው ወገነ የበላይነተ ሲጠናቀቅ ዓለም ከስጋት ትላቀቃለቸ የሚለው ሀሳብ ገዝፎ ተስተውሏል። ተጨባጭ እውነታው ግን ከዚህ የተለየና ፍጹም የበርካታ አገራትን ነባራዊ ሁኔታ እንዳልነበረ ያደረገ ክስተት ሆኖ ተስተውሏል። በአንድ ወቅት የተረጋጋ ፖለቲካና ኢኮኖሚ ሁኔታ ይስተዋልባቸው የነበሩ አገሮችና ህዝቦች ዛሬ በስም ብቻ የሚታወሱ ሆነዋል። አብዛኛዎቹም ግጭትና ጦርነት የዕለት ተዕለት መገለጫ ተግባራቸው ተደርጓል።
አገራቱን ለዚህ የዳረጋቸው ከተፈጥሮ ሃብት ሽሚያ እስከ ጂኦ ፖሊቲካዊ ፍላጎት የሚዘልቅ የውጭ ኃይሎች ጣልቃ ገብነት መሆኑ ሳይታለም የተፈታ ጉዳይ ነው። ምስቅልቅል ለሆነው ወቅታዊ ሁኔታቸው መነሻው ምንም ይሁን ትልቁን ድርሻ የሚይዘው በአገሮቹ ጉዳይ የውጭ ጣልቃ ገብነት ይዞት የሚመጣው ጦስ ነው። በዚህም ዜጎቻቸው ለሞት፣ ለስደትና ለጉስቁልና ተዳርገዋል።
በተለይ ሶማልያ፣ ኢራቅ፣ ሶሪያ፣ የመንና ሊቢያ እንዲሁም አፍጋኒስታንና ሱዳን የውጭ ኃይሎች ጣልቃ ገብነት ሰለባ በመሆን ሕዝቦቻቸው ለስቃይ የተዳረጉባቸው ናቸው። በእነዚህ አገራት የተካሄዱት የእርስ በርስ ግጭቶችና ጦርነቶች ለውጭ ኃይሎች የሃይል ሚዛን ማስከበሪያና የመሪነታቸውን ሚና ማረጋገጫ የእጅ አዙር የፍልሚያ ሜዳ ሆነዋል። አሁንም የየአገሮቹ ዜጎች ለከፋ ስቃይና ሞት፣ ስደት እየተዳረጉ መሆኑ እሙን ነው። በዚህ ውስጥ በቀዳሚነት ጣልቃ በመግባት የመሪነት ስፍራውን የያዘችው ደግሞ አሜሪካ ናት።
የእነዚህ አገራት ህዝቦች በራሳቸው የውስጥ ጉዳይ በፈጠሯቸው ግጭቶችና እርሱን ተከትሎ በተጀመረው ጣልቃ ገብነት ያተረፉት ነገር ቢኖር ሞት፣ ስደትና የልማት ተቋማት መውደም ብቻ ነው። በመሰረቱ የየአገሮቹ ዜጎች ስሜትን ሰቅዞ በሚይዝ ቅስቀሳ ተመርተው ወደ ግጭት የገቡት አገራቸው ወደ ፍርስራሽነት ተቀይረው የፍዳ ምድር እንዲሆኑ አልነበረም።
አገሮች የራሳቸውን የውስጥ ጉዳይ በራሳቸው እንዲፈቱ ከማድረግ ይልቅ ጣልቃ መግቢያ ቀዳዳ በመፈለግ እየገቡ የመበታተን፣ አገር የማጥፋት ተግባር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መምጣቱ በግል እየተስተዋለ ነው። ለዚህም የአገራችንን ሁኔታ በአብነት መጥቀስ እንችላለን።
በአሁኑ ወቅት በሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል የተፈጠረውን ግጭት ሰበብ አድርገው ጣልቃ ለመግባት እንደ እሳት እራት ዙሪያዋን የሚዞሯት የውጭ ኃይሎች ጫና ለመፍጠር ያልፈነቀሉት ድንጋይ የለም። ከዲፕሎማሲያዊ ጫና እስከ ኢኮኖሚያዊ ማዕቀብ፣ ከሀሰተኛ መረጃ እስከ መገናኛ ብዙሃን የተዛባና ሚዛኑን ያልጠበቀ ዘገባ ዘመቻ በማካሄድ በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ ለመግባት ረጅም ርቀት ተጉዘዋል።
የዚህ ዋነኛ ተዋናይ ደግሞ ኢትዮጵያ በአጋርነት የምትጠራቸው አሜሪካና የአውሮፓ ኅብረት ናቸው። የዚህ ዓይነቱ ድርጊት በብዙዎች ዘንድ አግራሞትን ፈጥሯል። በአፍሪካ ቀንድ የአሜሪካ ልዩ ልዑክ ጄፍሪ ፌልትማን ሰሞነኛ የአዲስ አበባ ጉብኝት አንድምታም የጣልቃ ገብነቱ ማሳያ ተደርጎ የሚወሰድ ነው።
በኢኮኖሚያዊ ማዕቀብ እና ዲፕሎማሲያዊ ጫና የታጀበው የአሜሪካ “የኢትዮጵያ ጉዳይ ያሳስበኛል” ማለት ጣልቃ ገብነቱን በዘዴ ለማስፈጸም የሚደረግ ሙከራ መሆኑ ግልጽ ነው። ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ ለመግባት የሚደረጉ ሙከራዎችን መንግሥት ፈጽሞ እንደማይቀበለው በቅርቡ በኒውዮርክ ከተማ በተካሄደው 76ኛው የመንግሥታቱ ድርጅት ጠቅላላ ጉባዔ ላይ ግልጽ አድርገዋል።
ኢትዮጵያ “የትኛውንም ጣልቃ ገብነት አልቀበልም” ያለችው ከዓለም አገራት ጋር በትብብር መስራትን ለመፃረር ሳይሆን በዋነኝነ የተፈጠረው ችግር የውስጥ ጉዳይዋ በመሆኑ ነው። በሌላ በኩልም በውጭ ጣልቃ ገብነት ምክንያት ኢራቅ፣ ሶሪያ፣ የመንና ሊቢያ አሁን ላይ ምን እንደሆኑ ጠንቅቃ ስለምትገነዘብም ነው።
ስለሆነም ኢትዮጵያ “ተጨንቀናል፣ አሳስቦናል፣ ተደራደሩ” በሚልና አሸባሪዎቹ ህወሃትንና ሸኔን ከመንግስት እኩል ለማድረግ የሚቃጣ የውጭ ጣልቃ ገብነትን በፍጹም የምትፈቅድበት መሰረት የላትም። አሁን የገጠማትን የህልውና አደጋ ለመቀልበስ ከሁሉም አቅጣጫ ሆ! ብሎ የተነሳው ህዘብ ይበልጥ በተደራጀና በተናበበ መልኩ ጦርነቱን በድል በማጠናቀቅና አደጋውን በመቀልበስ የውጭ ጣልቃ ገብነትን ሊያመክነው ግድ ይለዋል። የውጭ ጣልቃ ገብነትን ለመግታት አሁን የተጀመረውን ትግል በድል ማጠናቀቅ ያስፈልጋል። ኢትዮጵያዊያን ደግሞ ይህን ታሪካዊ ሃላፊነታቸውን በአኩሪ ተጋድሎ ይወጣሉ።