የኢትዮጵያ ዲያስፖራ የተግባር ምክር ቤት የውጭ ጣልቃ ገብነት ለመመከት በቁርጠኝነት እንደሚሰራ ገለጸ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ዲያስፖራ የተግባር ምክር ቤት የውጭ ጣልቃ ገብነት ለመመከት በቁርጠኝነት እንደሚሰራ ገለጸ
አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 27 /2014 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ ዲያስፖራ የተግባር ምክር ቤት በኢትዮጵያ ላይ እየተደረገ ያለውን ያልተገባ የውጭ ጣልቃ ገብነት ለመመከት በቁርጠኝነት እንደሚሰራ ገለጸ፡፡
ምክር ቤቱ ከጳግሜ 2013 ዓ.ም ጀምሮ በኢትዮጵያ ሲያካሄድ የነበረውን የጉብኝት ማጠቃለያ መርሃ ግብር አካሂዷል።
የምክር ቤቱ ዋና አስተባባሪ አቶ አለባቸው ታደሰ፤ የምክር ቤቱ አባላት ''እንቁጣጣሽ ኢትዮጵያ የፍቅር ጉዞ'' በሚል ሃሳብ አገር ውስጥ መግባቱን አስታውሰዋል።
ምክር ቤቱ ጉዞውን ያደረገው በተለይም በኢትዮጵያ የህልውና ዘመቻ እየተካሄደ ባለበት ወቅት ከመሆኑ ጋር ተያይዞ የመከላከያ ሰራዊቱን ማበረታታትና ድጋፍ ማድረግ ዋነኛ ስራው አድርጎ መንቀሳቀሱንም ተናግረዋል፡፡
በተጨማሪም በገበታ ለሀገር የተካተቱ የቱሪዝም መስኮችን በመጎብኘት በቀጣይ የሚጠበቅበትን ድጋፍ ለማድረግ የቤት ስራ ውስዷል ነው ያሉት፡፡
የህዳሴ ግድብ በመጎብኘት ፣በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር በመሳተፍና ለመከላከያ ሰራዊቱ ደም በመለገስ የተሳካ ቆይታ ማድረጋቸውንም ጨምረው ገልጸዋል፡፡
በዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ስለ ኢትዮጵያ የሚናገረውና በኢትዮጵያ ላይ በተግባር ያለው ሁኔታ የተለያየ መሆኑን አንስተው፤ ምክር ቤቱ በኢትዮጵያ ያለውን እውነት ለማሳወቅ እንደሚሰራ ተናግረዋል፡፡
በኢትዮጵያ ላይ እየተደረገ ያለውን ያልተገባ የውጭ ጣልቃ ገብነት ለመመከት በቁርጠኝነት እንደሚሰራም ጨምረው ገልጸዋል፡፡
በኢትዮጵያ እያደገ የመጣውን የቱሪዝም ልማት ለመደገፍ የበኩላቸውን ሚና እንደሚወጡም እንዲሁ፡፡
በተያያዘ በተለያዩ የዓለም አገራት የሚኖሩ የምክር ቤቱ አባላት በሙያቸው አገራቸውን በበጎ ፈቃድ እንዲያገለግሉ ለማድረግ እንቅስቃሴ መጀመሩንም አመላክተዋል።
ምክር ቤቱ በኢትዮጵያ ቆይታው ድጋፍ ላደረጉለት ተቋማትና ግለሰቦች የምስጋናና የእውቅና ሰርተፍኬት አበርክቶላቸዋል፡፡
የኢትዮጵያ ዲያስፖራ የተግባር ምክር ቤት መቀመጫውን ሰሜን አሜሪካ ያደረገ ሲሆን በ20 አገራት ባሉ ጽህፈት ቤቶቹ በርካታ አባላት ያሉትና ለትርፍ ያልተቋቋመ ድርጅት ነው።