ቀጥታ፡

የአሸባሪውን ህወሓት ሀገር የመበተን ህልም ለማክሸፍ መላው ህዝብ በተደራጀ አግባብ እንዲታገል ጥሪ ቀረበ

ሐዋሳ፤ ጥቅምት 27/2014 (ኢዜአ)፡ የአሸባሪውን ህወሓት ሀገር የመበተን ህልም ለማክሸፍ መላው የክልሉ ሕዝብ በተደራጀ አግባብ እንዲታገል የደቡብ ክልል ብልጽግና ፓርቲ ጥሪ አቀረበ ።

የፓርቲው ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ጥላሁን ከበደ በወቅታዊ ጉዳይ ላይ ዛሬ ለመገናኛ ብዙሃን በሰጡት መግለጫ እንዳሉት ለዓመታት ኢትዮጵያን ለመበታተን ሲሠራ የቆየው አሸባሪው ህወሓት ህልሙን ለማሳካት ባለ በሌለ ኃይል እየተንቀሳቀሰ ነው።

ለዚህ እንዲረዳውም እንደ አሸባሪው ሸኔ ያሉ  ለሆዳቸው ያደሩ፣ ምን ዓላማ እንዳላቸው በግልፅ የማይታወቅ  የውስጥ ተላላኪዎችንና ከኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶች ጋር በትብብር እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

ህወሓት ኢትዮጵያን በማፍረስ ታላቋን ትግራይ ለመገንባት ይህ ካልሆነም ዳግም ስልጣንን  በመቆናጠጥ በህዝቡ ላይ የጭቆና ቀንበር ለመጫን ዓልሞ እየሠራ ነው ብለዋል ።

በተለይ አሸባሪው ህወሓት በስልጣን በቆየባቸው ዓመታት  በሰራው የኢኮኖሚ አሻጥር ክልሉ እንዲጎሳቆል፣  የክልሉ ኢንቨስትመንት በትግራይ ተወላጆች እንዲያዝ በማድረግ የማዳከምና የሥራ ዕድሎች እንዲመክኑ  ማድረጉን አስታውሰዋል።

የክልሉ የቡና ምርት በትግራይ ክልል ተወላጆችና በደጋፊዎቹ ብቻ እንዲያዝ በማድረግ ጅማና ሚዛን ቴፒ ከተሞች እንዲጎሳቆሉ ማደረጉን ጠቁመዋል።

ወላይታ ሶዶ፣ ተርጫና ሌሎች አየር ማረፊያ የነበራቸው ከተሞች መሰረተ ልማቶች እንዲዘጉ በማድረግ በከተሞች እድገት ላይ አሉታዊ ተዕኖ ማሳረፉን አመልክተዋል።

በደርግ ሥርዓት በክልሉ የተቋቋሙ ፋብርካዎችን  ነቃቅሎ በመውሰድ አካባቢው በአለው የመልማት አቅም እንዳያድግ ማድረጉን ገልጸዋል።

የአርባ ምንጭና ሀዋሳ ጨርቃ ጨርቅ ፋብርካዎችን  የውስጥ አካል ነቅሎ በመውሰድ አሁን ለወንጀል የጥፋት ተልዕኮ የዋለውን  መቐለ አልመዳ ፋብርካን መክፈቱን ገልጸዋል ።

ለዘመናት ተሳስቦና ተፈቃቅሮ የኖረውን የክልሉ ማህበረሰብ ብዝሃነትን  እንደ እርግማን በመስበክ እርስ በርስ ተግባብቶ እንዳይኖር ማድረጉን አብራርተዋል ።

አሸባሪወ ህወሓት የትግራይን ህዝብ በሀሰት ትርክት በማዕበል መልክ በማሰለፍ፣ የሀሰት ፕሮፖጋንዳ የሚያሰራጩ አካላትንና ተላላኪዎቹን በአካባቢው በማደራጀት ሀገር ለማፍረስ እየተንቀሳቀሰ ነው።

የአሸባሪውን ህልም ለማምከን መላው የክልሉ ህዝብ በየአካባቢው በህዝባዊ ሠራዊት ስሜት በመነሳሳት፣ ጠላትን ማጥራትና መከላከያን በመደገፍ በህልውና ዘመቻ ላይ እንዲሳተፍ ጥሪ አቅርበዋል።

ዛሬ በክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች ሀገር የማዳን ዘመቻና የድጋፍ ሰልፍ መካሄዱን የገለጹት አቶ ጥላሁን ይሄም ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።

ለሀገር መከላከያ ሠራዊት ድጋፍ ከ250 ሚሊዮን በላይ ገንዘብ መሰባሰቡን የተናገሩት ኃላፊው፤ የስንቅ ዝግጅት መጀመሩን ገልጸዋል።

አቅሙ የቻለ የክልሉ ነዋሪ ወደ ግንባር ለመዝመት መዘጋጀት እንዳለበት አስገንዝበዋል።

በክለሉ በተለያዩ የአካባቢዎች የአሸባሪው ህወሓት ተላላኪዎችና ሰርጎ ገቦች እንዳሉ በክትትል መረጋገጡን ያሳወቁት አቶ ጥላሁን መላው የክልሉ ህዝብ ከፀጥታ አካላት ጋር በመተባበር አካባቢውን በንቃት እንዲጠብቅ ጥሪ አቅርበዋል።

የክልሉ ነዋሪ የሕልውና ዘመቻውን ከመደገፍ ጎን ለጎን የልማት ስራዎችን ጠንክሮ እንዲሰራም አሳስበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም