ቀጥታ፡

የአሜሪካ መንግሥት በኢትዮጵያ ላይ የጣለው ማዕቀብ በሕዝብ ይሁንታ ወደ ሥልጣን የመጣውን መንግሥት እውቅና ለመንፈግ ነው

ጥቅምት 27/2014 (ኢዜአ) የአሜሪካ መንግሥት በኢትዮጵያ ላይ የጣለው ማዕቀብ በሕዝብ ይሁንታ ወደ ሥልጣን የመጣውን መንግሥት እውቅና ለመንፈግ ያለመ ነው ሲሉ ዓለም አቀፍ የፖለቲካል ኢኮኖሚና ደኅንነት ምሁራን ተናገሩ።

የአፍሪካ የፖለቲካ-ኢኮኖሚ ተንታኙ ፕሮፌሰር ላውረንስ ፍሪማን እንደገለጹት፤ አሜሪካ ኢትዮጵያን በተመለከተ የምታራምደው አቋም የኢትዮጵያን ሕዝብ የሚጎዳ ነው።

ይህም በሕዝብ ይሁንታ ወደ ሥልጣን የመጣውን በጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ የሚመራውን መንግሥት እውቅና ለመንፈግ ያለመ ነው ብለዋል።

በአንጻሩ አሜሪካ አሸባሪውን የሕወሃት ቡድን የሚነቅፍ አቋም አለማንጸባረቋን ገልጸው ይህም ለኢትዮጵያ ሕዝብ ጉዳት መሆኑን ነው ፕሮፌሰሩ ለኦ ቢ ኤን በሰጡት ቃለ ምልልስ ያረጋገጡት።   

አሜሪካና አንዳንድ የምዕራቡ ዓለም አገራት በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ ላይ ጭፍን ጥላቻ እያራመዱ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በየአካባቢው የተደራጁ አማጽያኖች እንዲበራከቱና መንግሥትን እንዲወጉ በማድረግ ኢትዮጵያ ተበታትና የማየት ፍላጎት እንዳላቸው በግልጽ ታይተዋል ብለዋል።

አሁን ሥልጣን ላይ ያለው መንግሥት በሕዝብ የተመረጠ መሆኑን ገልጸው የአሜሪካ መንግሥት ሽብርተኛውን ሕወሃት ከመደገፍ ይልቅ ሕዝባዊ ቅቡልነት ያለውን መንግሥት መደገፍ አለባት ነው ያሉት።

አሜሪካ በጆ ባይደን የሥልጣን ጊዜ በአፍሪካ ቀንድ ያላትን ተጽዕኖ እያጣች መሆኗን ገልጸው “አሁን ደግሞ የቀጠናው የረጅም ጊዜ አጋር የሆነቻትን ኢትዮጵያ ካጣች በአፍሪካ ያላትን ተሰሚነት በእጅጉ ያሳጣታል” ብለዋል።

አሜሪካ ያሳለፈችው ኢትዮጵያን ከቀረጥ ነፃ እድል (አጎዋ) ተጠቃሚነት እንድታጣ ያሳለፈችውን አይነት ውሳኔ ካስቀጠለችም ለኢትዮጵያ ጎጂ መሆኑን ተናግረዋል።

ስለሆነም ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ለመላው አፍሪካ ጥቅም ሲባል አሜሪካ እየተከተለች ያለውን የተሳሳተ ፖሊሲ በአስቸኳይ በመቀልበስ ማሻሻል አለባት ብለዋል።

በተለይም ደግሞ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ የሚመራውን መንግሥት መደገፍ እንዳለባት ተናግረዋል።

አሸባሪው ህወሃት በኢትዮጵያ ላይ ጦርነት መክፈቱ እየታወቀ ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙኃን የተሳሳተ ዘመቻ በመክፈት ገለልተኛ አለመሆናቸውን አረጋግጠዋልም ብለዋል።

ዓለም አቀፍ የፀጥታ ባለሙያው ፕሮፌሰር አን ፊትዝ ጄራልድ በበኩላቸው አሜሪካ ኢትዮጵያ ከቀረጥ ነፃ እድል (አጎዋ) ተጠቃሚ እንዳትሆን ማገዷ ኢትዮጵያ ላይ አላስፈላጊ ጫና ለማድረግ ነው ብለዋል።

በተለይም ደግሞ የጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ መንግሥት ከሽብርተኛው የሕወሃት ቡድን ጋር ለማደራደር ያለመ መሆኑን በመጠቆም።

አሜሪካ እየወሰደች ያለው የቅጣት እርምጃም ወደ አንድ ወገን ያደላ ስለመሆኑ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ መንግሥትም ሽብርተኛው የሕወሃት ቡድን የከፈተውን ጦርነት በመቀልበስ ለዜጎቹ ሰብዓዊ ድጋፍ ማድረግ የሚያስችል ተግባራትን ማከናወኑን አመላክተዋል።

"ኢትዮጵያዊያን የሚያስተዳድራቸውን መንግሥት በዴሞክራሲያዊ መንገድ መርጠዋል፤ በሕወሃት  የአምባገነንነት ሥርዓት ዳግም ለመተዳደር ፍላጎት የላቸውም" ብለዋል።

በኢትዮጵያ በተካሄደው አገራዊ ምርጫ ፍትሃዊና ነጻ በአገር ውስጥና በዓለም አቀፍ ታዛቢዎች ነጻና ፍትሃዊ መሆኑን መረጃ ጠቅሰውም ሃሳባቸውን አጠናክረዋል።

የምዕራባውያን መገናኛ ብዙሃንና ግብረሰናይ ድርጅቶች አመጹን ከማባባስ ይልቅ በአማራ ክልል ለመሥራት ፈቃደኛ አለመሆናቸውን ታዝቤያለው ብለዋል።

"ግብረሰናይ ድርጅቶቹና ቡድኖች በዛቻ እና ማስፈራሪያ እንደሚሰሩ ጥርጥር የለኝም" ያሉት ፕሮፌሰሯ ምናልባትም በአማራና አፋር ክልሎች ያልተሰማሩበት አንዱ ምክንያትም ይህ ሊሆን እንደሚችል ገምተዋል።

ያም ሆኖ በአሸባሪው የህወሃት ወራሪ ኃይል አሁንም ወጣቶችና በሁሉም የእድሜ ክልል እየገደለ እንደሚገኝ፣ ንብረቶችና የንግድ ድርጅቶች በመዘረፍና የእርሻ ሰብልም በማውደም ላይ መሳተፋቸውን ጠቁመዋል።

"ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብም በአሸባሪው የሕወሃት መሪዎች ላይ የቅጣት እርምጃ መውሰድ አለበት" ሲሉ አጽንኦት ሰጥተዋል።

በአሁኑ ወቅትም አሸባሪው የህወሃት ኃይል እካሄደ ያለውን ጥፋት ማስቆም ካልተቻለ ምስራቅ አፍሪካንም አደጋ ውስጥ እንደሚጥል ስጋታቸውን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም