ቀጥታ፡

የምንዘምተው አሸባሪውን ደምስሰን በድል ለመመለስ ነው

ጥቅምት 27/2014 (ኢዜአ) አሸባሪውን ህወሃት ደምስሰው በድል በመመለስ አገርን ለማስቀጠል እንደሚዝምቱ የሸገር የብዙሃን ትራንስፖርት አገልግሎት ድርጅት ሰራተኞች ገለጹ።

እኛ እያለን ኢትዮጵያ አትፈርስም በማለት በአገር ላይ የተቃጣውን የህልውና አደጋ ለመመከት ተቋማት ለሀገራዊ ጥሪው መልስ እየሰጡ ይገኛሉ፤ ሸገር የብዙሃን ትራንስፖርት አገልግሎት ድርጅትም ለዘማች ሰራተኞቹ ሽኝት አድርጓል።

የቀድሞ ሰራዊት አየር ወለድ የነበሩት ሻምበል ዘውዱ ወልደሃና ወራሪው ቡድን ያደረሰው ግፍና ያሳየው ንቀት አስቆጥቷቸው አገሪቷ ያቀረበችውን ጥሪ በመቀበል መስዋእት ለመሆን ሳይሆን ድል አድርገው ለመመለስ እንደሚዘምቱ ገልጸዋል።

በጨቋኝ መሪ፣ በከፋፋይ አስተሳሰብ የምትመራ ኢትዮጵያን ለልጆቼ ከማወርስ እኔ ሻማ ሆኜ ሉአላዊት የሆነች ኢትዮጵያን ማስረከብ ኩራቴ ነው ብለዋል።

ወጣት እታበዝ ይፍሩ ''ጾታ ሳይገድበኝ ሀገሬ ያቀረበችልኝን ጥሪ ተቀብዬ መከላከያ ሰራዊቱን ለመቀላቀል ወሰኛለሁ'' በማለት ሃገር ስትፈርስ ከማየት በላይ ህመም አለመኖሩ ለውሳኔ እንዳበቃት ተናግራለች።

ሌላኛው ዘማች ወታደር ማስረሻ ሱሪ ነፍሰጡር ሚስቱን በመተው ለመዝመት መወሰኑን ገልጿል፤ ''ሃገር በሌለችበት የሚወለድ ልጅ የት ሊያድግ ይችላል?'' በማለት ቤተሰቡን ለድርጅቱ ሰጥቶ ለሃገር ህልውና ሊዘምት መነሳቱን ተናግሯል።

በሽኝቱ ላይ የተገኙት የፌዴራል ፖሊስ የትራንስፖርት ሃላፊ ኮማንደር መርጋ አለማየሁ ባለፈው ዓመት ጥቅምት 24 የህወሃት ቡድን በጀግናው መከላከያ ሰራዊት ላይ ያደረሰው ክህደት ሃገር ይቅር የማይለው እንደሆነ አስታውሰው ሁሉም ኢትዮጵያዊ ለሃገሩ ጥሪ ምላሽ የሚሰጥበት ጊዜው አሁን ነው ብለዋል።

ወራሪው ቡድን ሃገር አንድ ሆና እንዳትቀጥል ቢያሴርም ኢትዮጵያዊያን በተባበረ ክንድ ወራሪውን እየመከቱ እንደሚገኙ ተናግረዋል።

ድርጅቱ መከላከያ ሰራዊቱን ለተቀላቀሉ ዘማቾች ደመወዛቸውን ከነሙሉ ጥቅማጥቅም ለቤተሰቦቻቸው እንደሚሰጥ፣ ለዘማች ቤተሰቦች የነጻ የትራንስፖርት እድል እንደሚያመቻችና ዘማቾች በተቋሙ ያለባቸውን እዳ ሙሉ በሙሉ እንደሚሰርዝ የድርጅቱ ስራ አስኪያጅ አቶ ቢተው ደመላሽ ተናግረዋል።

በተጨማሪም ዘማቾቹ በድል ሲመለሱ በድርጅቱ ውስጥ የተሻለ ቦታ እንደሚሰጣቸውና ለአንድ የዘማች ቤተሰብ አባል የነጻ የመንጃ ፈቃድ ትምህርት ለመስጠት ድርጅቱ በማኔጅመንት መወሰኑን ተናግረዋል።

ሸገር የብዙሃን ትራንስፖርት አገልግሎት ድርጅት ካሁን ቀደም ከ6ነጥብ 4 ሚሊዮን ብር በላይ ለመከላከያ ሰራዊት ድጋፍ ማድረጉን አስታውሰው በዛሬው እለትም 2 ሚሊዮን ብር ተጨማሪ ድጋፍ እንደሚያደርግ ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም