ቀጥታ፡

አሸባሪው ህወሓት በተባበረ ክንድ ይደመሰሳል

አሶሳ ፤ ጥቅምት 27/2014 (ኢዜአ) አሸባሪው ህወሃት በየትኛውም የውጪ አካል ቢደገፍም በኢትዮያውያን የተባበረ ክንድ መደምሰሱ አይቀርም ሲሉ የአሶሳ ነዋሪዎች ተናገሩ፡፡

የኢትዮጵያ ህዝብ ለመጉዳት ለአሸባሪው ቡድን  የሚደረግ የውጭ ድጋፍ እንዲቆምም  ተጠይቋል፡፡

ከአሶሳ ነዋሪዎች መካከል መቶ አለቃ ድንበሩ ካብትይመር፤ አሸባሪው ህወሓት ኢትዮጵያውያንን በዘር በመከፋፈልና ልዩነትን በማስፋት አንድ ሆነን በሀገራቸን  እድገት ላይ የድርሻችንን እንዳናበረክት አድርጓል ሲሉለኢዜአ በሰጡት አስተያየት ገልጸዋል።

ህወሓት ኢትዮያውያንን እየሞቱ እና በድህነት እንዲቀጥሉ ምኞቱን ለማሳካት ከውጭ በሚደረግለት ድጋፍ የጥፋት ተግባሩን እንደቀጠለበት አመልክተዋል፡፡

ነጻነት በልመና አይገኝም፤ ኢትዮጵያዊያን ለጠላት በራችንን ሳንከፍት በአንድ ልብ እና ቋንቋ መታገል አለብን ብለዋል መቶ አለቃ ድንበሩ፡፡

አሸባሪው ህወሃት በየትኛውም የውጭ ሃይሎች ቢደገፍም የጊዜ ጉዳይ ካልሆነ በቀር መደምሰሱ አይቀርም ፤ ሀገርን ለማዳን ለሚቀርብ ጥሪ የትኛውንም መስዋዕትነት ለመክፈል ዝግጁ ነኝ ሲሉ አስታውቀዋል፡፡

በቅርቡ በሀገር ደረጃ  የታወጀው የአስቸኳይ  ጊዜ አዋጅ ህወሃትን ጨምሮ ሌሎችም ሃገር እያመሱ የሚገኙ የጸረሠላም ሃይሎችን እንቅስቃሴ በተደራጀ አግባብ አደብ ለማስገዛት እንደሚበጅ የገለጹት ደግሞ  አቶ አብዱልቃሲም መሃጁብ ናቸው፡፡

ከተሳሳቱ ጥቂት ሰዎች በስተቀር ሁሉም ኢትዮጵያውያን የሀገሩ ሠላም ወደ ቀደመ ሁኔታው እንዲመለስ በጽኑ እንደሚፈልግ  እምነታቸው መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ከዚህ ቀደም ለአካባቢው ሠላም ሃላፊነቴን ስወጣ ቆይቻለሁ፤  ሠላም ከሌለ ሃገር እንደማትቀጥል በሚገባ እረዳለሁ ብለዋል፡፡

ህብረተሰቡን በማስተባበር በየአካባቢው የጥፋት ቡድኖችን እንቅስቃሴ ከመቆጣጠር ባለፈ ሀገርን ለማዳን በግንባር በመሰለፍ የድርሻቸውን ለመወጣት መዘጋጀታቸውን አስታውቀዋል፡፡

አቶ ማርቆስ ፍራንኮ የተባሉ ነዋሪ በበኩላቸው፤ አሸባሪው  የህወሃት ቡድን ለ27 ዓመታት ኢትዮጵያን ያለከልካይ ዘርፏል ብለዋል፡፡

ቡድኑ በዚህ ሳያበቃ የማይነካውን የሰሜን ዕዝ ከጀርባው ጥቃት እንደፈጸመበት አስታውሰው፤ የሽብር  ድርጊት አሰቃቂ ቢሆንም ኢትዮጵያን ማፍረስ አይችልም ነው ያሉት፡፡

አባቶች መስዋዕትን ከፍለው ያስረከቡንን  ሃገር ለማስቀጠል ከመከላከያ ሰራዊት ጎን  በግንባር አሸባሪው ቡድን  ለመፋለም ዝግጁ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

የውስጥ ባንዳዎችም ሆኑ አንዳንድ የምዕራባዊያን ሀገራት አሸባሪው  ህወሃት ወደ ስልጣን ለማምጣት ቢደግፉም ቡድኑ መወገዱ እና ኢትዮጵያም መቀጠሏ እንደማይቀር ሊረዱ ይገባል ብለዋል፡፡

ኢትዮጵያን ለማፍረስ የሚሯሯጡን የጥፋት ቡድኖች እንደሚቃወሙ  የገለጹት  አቶ ሹማ አያና በበኩላቸው፤ ኢትዮጵያ ከሌለች ተተኪ ዜጎች የሉንም፤  በግንባር ተሰልፌ አሸባሪውን መዋጋት እፈልጋለሁ ሲሉ አስታውቀዋል።

በመስዋዕትነታችን ኢትዮጵያ ትቀጥላለች ሲሉ አክለዋል፡፡

ሌላው የከተማው ነዋሪ አቶ አሸናፊ ወንድሙ፤  ጥቂት የአሸባሪው ህወሃት ቡድን አባላትን ለማዳን እና ከ115 ሚሊዮን በላይ የኢትዮጵያ ህዝብ ለመጉዳት የሚደረግ የትኛውም  የውጭ ድጋፍ እንዲቆም ጠይቀዋል።

ሀገር ሲፈርስ ቆሞ የሚያይ የለም፤ ወልደን መሳምም ሆነ ሰርተን የምንቀየረው በሀገር ነው ያሉት ነዋሪው ወደ ግንባር ዘምተው አሸባሪውን መዋጋት እንደሚፈልጉ ገልጸዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም