በድሬደዋ ከህወሃት እና ሸኔ ጋር ግንኙነት የነበራቸው ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ሥር ዋሉ - ኢዜአ አማርኛ
በድሬደዋ ከህወሃት እና ሸኔ ጋር ግንኙነት የነበራቸው ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ሥር ዋሉ

ድሬደዋ ፤ ጥቅምት 27/2014(ኢዜአ) በድሬዳዋ አስተዳደር ከአሸባሪዎቹ ህወሃት እና ሸኔ ጋር ግንኙነት የነበራቸው ተጠርጣሪዎች ከተለያዩ የጦር መሳሪዎችና ሌሎች ቁሳቁሶች ጋር በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን ፖሊስ አሰታወቀ።
በቁጥጥር ስር በዋሉት ላይ ምርመራ መጀመሩም ተመልክቷል፡፡
የድሬዳዋ አስተዳደር ፖሊስ የህዝብ ግንኙነት እና ለውጥ ስራ ዳይሬክተር ኮሎኔል ገመቹ ካቻ ዛሬ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ ፤ ተጠርጣሪዎቹ በቁጥጥር ሥር የዋሉት በድሬዳዋ በሚገኙ ሁሉም ቀበሌዎች ከጥቅምት 25/2014 ዓ.ም. ጀምሮ ለሁለት ቀናት በተካሄደ ኦፕሬሽን እንደሆነ ተናግረዋል።
በዚህም ከህወሃት እና ሸኔ ጋር ግንኙነት የነበራቸው ተጠርጣሪዎች የተያዙ ሲሆን መኖሪያ ቤቶች ውስጥ በተደረገ ብርበራ ሽጉጦች ከመሰል ጥይቶች ጋር ፣ የተለያዩ መጠን ያላቸው የኢትዮጵያ እና የውጭ ሀገር ገንዘቦች እንደተገኘባቸው አመልክተዋል።
እንዲሁም ፈንጂ ማቀጣጠያ ገመዶች ፣ የደንብ ልብስ እና ትጥቆች፣ ተንቀሳቃሽ ሞባይል፣ ላፕቶፕኮምፒተሮች፣ፓስፖርት ፣የጦር ሜዳ መነጽር፣ መቅረጸ- ድምጽ፣ አደንዛዥ እጽ ማህተሞች፣ እና የተለያዩ ሰነዶች በቁጥጥር ስር ውለዋል፡፡
የድሬዳዋ ከተማን ጸጥታ ለማረጋገጥ ፖሊስ ከጸጥታ አካላት እና ህብረተሰብ ጋር የተቀናጀ ስራ በመከናወኑ አመርቂ ውጤት መገኘቱን ኮሎኔል ገመቹ አስረድተዋል፡፡
በአገራችን ላይ የውስጥም ሆነ የውጭ ጸረ-ሰላም ሃይሎች የከፈቱብንን ጦርነት ለማምከን የድሬዳዋ ህብረተሰብ አካባቢውን በሚገባ በመጠበቅ ከጸጥታ አካላት ጋር ተቀናጅቶ መስራት አለበት ብለዋል።
የህወሃት እና ሸኔ አገር የማፍረስ ምኞትን ለማክሸፈ በሚደረገው ሁሉ አቀፍ እንቅስቃሴ ሁሉም የድሬዳዋ ነዋሪ መሳተፍ እንዳለበትም አመልክተዋል፡፡
የድሬዳዋ ፖሊስ ከመቼውም ጊዜ በላይ የከተማውን ሰላምና ጸጥታ ለማስከበረ እየሰራ መሆኑን የገለጹት ኮሎኔል ገመቹ፤ ህብረተሰቡም በአካባቢው አጠራጣሪ ነገሮችን ሲመለከት በአቅራቢያው ለሚገኝ የፖሊስ አባል ወይም በፖሊስ የመረጃ ስልክ ቁጥሮች 0251111600 ወይም 0251115211 ላይ በመደወል የዜግነት ግዴታውን እንዲወጣም አሳስበዋል፡፡