የክተት ጥሪውን ተቀብለን ለመዝመት ተዘጋጅተናል - ኢዜአ አማርኛ
የክተት ጥሪውን ተቀብለን ለመዝመት ተዘጋጅተናል
ሀዋሳ፤ ጥቅምት 27/2014 (ኢዜአ) ሀገርን ለማዳን የተላለፈውን የክተት ጥሪውን ተቀብለው ለመዝመትና አስፈላጊውን መስዋዕትነት ለመክፈል መዘጋጀታቸውን የሀዋሳ ከተማ ነዋሪዎች አስታወቁ።
መንግስት በሀገር ላይ የተደቀነውን የህልውና አደጋ ለመቀልበስ ያስተላለፈውን የክተት ጥሪ አስመልክቶ ኢዜአ ያነጋገራቸው የሀዋሳ ከተማ ነዋሪዎች በሰጡት አስተያየት፤ ከፀጥታ አካላት ጋር በመቀናጀት የአካባቢያቸውን ሰላም በመጠበቅ ጭምር ኢትዮጵያን ለማዳን እንደተነሳሱ ገልጸዋል
ከነዋሪዎቹ መካከል ወጣት ተመስገን አድንቀው፤ ''የሀገርን ህልውና የማስጠበቅ ተግባር ለመንግስትና ለመከላከያ ሰራዊት የምንተወው ጉዳይ ባለመሆኑ እያንዳንዳችን ከእኔ ምን ይጠበቃል በሚል እሳቤ ግዴታችንን መወጣት አለብን'' ብሏል።
''ሀገሬን ለማዳን እስከግንባር ድረስ በመሄድ መስዋዕትነት ለመክፈል ዝግጁ ነኝ'' ያለው ወጣቱ፤ በሰሜን ኢትዮጵያ አሸባሪው ቡድን በዜጎች ላይ እያደረሰ ያለው ጉዳት የሁሉም ዜጋ ችግር በመሆኑ እንደ አንድ ቤተሰብ በማሰብ መዝመት እንደሚያስፈልግ ተናግሯል።
አሸባሪው ህወሓት ዋነኛ የጦር ስትራቴጂው የሀሰት ፕሮፖጋንዳ በመሆኑ የተለያዩ የሚዲያ አማራጮችን በመጠቀም ህዝብን የሚያሸብሩ የተዛቡ መረጃዎችን እንደሚያስተላልፉ ገልጾ፤ ሁሉም ሰው በአሸባሪው ቡድን የሀሰት መረጃ ሳይደናገር አካባቢውን በንቃት በመጠበቅ አጠራጣሪ ጉዳዮችን ለፀጥታ አካላት በመጠቆም የድርሻውን መወጣት እንዳለበትም አመልክቷል።
ህወሓት በሚያሰራጨው የሀሰት መረጃ ዓለም ዓቀፉን ማህበረሰብ እያሳሳተ ቢሆንም ኢትዮጵያውያን ወደ ጦርነት የገቡት እውነትን ይዘው በመሆኑ ድሉ የኢትዮጵያ ነው ያለው ደግሞ ወጣት አብዱልረዛቅ ሸምሱ ነው።
''በሠላም ሰርቼ የምኖረው ሀገሬ ስትኖር ነው'' ያለው ወጣት አብዱልረዛቅ፤ በሀገር ላይ የተቃጣውን ጦርነት ለመመከት እስከ ግንባር ድረስ ዘምቶ ለመዋጋት መዘጋጀቱን አስታውቋል።
ሌላው የከተማው ነዋሪ አቶ ስምዖን ከተማ በበኩላቸው፤ ከዚህ ቀደም የአንድ ወር ደመወዛቸውን ለሀገር መከላከያ ሰራዊት ድጋፍ ማድረጋቸውን አስታውሰዋል።
''ለሀገሬ የማደርገው ድጋፍ ገንዘብ በመስጠት ብቻ ተወስኖ አይቀርም'' ያሉት ነዋሪው፤ ግንባር ድረስ በመዝመት ባላቸው የመካኒክነትና የሹፍርና ሙያ ለማገልገል ቁርጠኛ መሆናቸውን ተናግረዋል።
''አሸባሪው ህወሀት በሥልጣን ዘመኑ እርስ በአርስ ሲያባልን ቢቆይም ሀገራችንን በመንካቱ ዳግም አንድ የምንሆንበትን ዕድል ፈጥሮልናል'' ያለት አቶ ስምዖን፤ ቡድኑ ተደምሰሶ ኢትዮጵያ ወደ ሠላሟ እንዲመለስ አንድነትን አጠናክሮ ማስቀጠል እንደሚገባ አመልክተዋል።
ነዋሪዎቹ የክተት የጥሪውን ተቀብለው በመዝመት አስፈላጊውን መስዋዕትነት ለመክፈል መዘጋጀታቸውንና እስከዚያም ከፀጥታ አካላት ጋር በመቀናጀት የአካባቢያቸውን ሰላም ነቅተው እንደሚጠብቁ ገልጸዋል።