የጋምቤላ ከተማና አካባቢው ነዋሪዎች የውጭ ኃይሎችን ጫናና አሽባሪውን ህወሓት ተቃወሙ - ኢዜአ አማርኛ
የጋምቤላ ከተማና አካባቢው ነዋሪዎች የውጭ ኃይሎችን ጫናና አሽባሪውን ህወሓት ተቃወሙ
ጋምቤላ ፤ጥቅምት 27/2014(ኢዜአ) የጋምቤላ ከተማና አካባቢው ነዋሪዎች የውጪ ኃይሎች ጫናና አሸባሪው ህወሓት በማውገዝ ዛሬ ሰላማዊ ሰልፍ አካሄዱ።
ነዋሪዎቹ የድጋፍ ሰልፉን ያካሄዱት ’’የህወሓት የሽብር ቡድን የአማራና የአፋር ህዝቦች ጠላት ብቻ ሳይሆን የኢትዮጵያ ጠላት ነው!፣ አካባቢያችን ነቅተን እንጠብቃለን!፣ወደ ግንባር እንዘምታለን!''እና ሌሎችንም መፈከሮች በማንገብና በማሰማት ነው።
ከሰልፉ ታደሚዎች መካከል ወጣት ኮር ጆሽዋ በሰጠው አስተያየት የሰልፋ ዓላማ የኢትዮጵያ ነቀርሳ የሆነው ሽብርተኛው ህወሓት በአማራና በአፋር ክልሎች በንጸሃን ኢትዮጵያውያን ላይ የደረሰውንና እያደረሰ ያለውን ኢ-ሰብዓዊ ድርጊቶች ለማውገዝና የውጭ ሀይሎችን ጫና ለመቃወም ነው ብለዋል።
አሸባሪው ህወሓት እየፈፀማቸው ባሉ አረመኔያዊ ድርጊቶች በመቆጨትም የክልሉ ሕዝብ ከመከላከያ ሠራዊት ጎን መሆኔን ለማረጋገጥ በሰልፉ ተሳትፌያለሁ ብለዋል።
አሸባሪው ህወሓት እየተፈጸመ ያለውን ሀገር የማፍረስ ሴራ ለመመከት የሀገር መከላከያ ሠራዊትን ለመቀላቀል ዝግጁ መሆኑን የገለጸው የሰልፉ ታዳሚ ወጣት ኡቻን ኡገኔ ነው።
ሌለው የሰልፉ ተሳታፊ አቶ ደገፉ ዳንኤል በሰጡት አስተያየት ሽብር አራማጆቹ ህወሓትና ሸኔ በንጹሃን ወገኖቻችን ላይ በሚፈጽሟቸው አስከፊና ዘግናኝ ድርጊቶች መቆጨታቸውን ተናግረዋል።
በመሆኑም ጀግኖች አባቶች ያቆይዋትን ሀገር የመጠበቅ ኃላፊነት ለመወጣት ወደ ግንባር ለመዝመት ተዘጋጅቻለሁ ብለዋል።
የከልሉ ርዕስ መስተዳድር አቶ ኡሞድ ኡጁሉ በዚሁ ጊዜ ባስተላለፉት መልዕክት አሸባሪው ህወሓት ባለፉት 27 ዓመታት በዜጎች ላይ ሲፈጽማቸው የነበሩት ግፍና በደል አልበቃው ብሎት አሁንም አረመኔያዊ ድርጊቱን መቀጠሉን አመልክተዋል።
በተለይም በአማራና አፋር ክልሎች በሰብዓዊ ፍጡር ብቻ ሳይሆን፤ የቤት እንስሳትን ጭምር ከሰብዓዊ ፍጡር በማይጠበቅ መልኩ ጭካኔ በተሞላበት ሁኔታ እየገደለ መሆኑም ተናግረዋል።
ይህን መሰሉን ድርጊት እየፈጸመ ያለውን የሽብር ቡድን አሜሪካና ምዕራባዊያን የተገላቢጦሽ በመንግሥት ላይ እያደረሱት ያለው ጫና ኢትዮጵያ ጠልነታቸውን በገሃድ ማሳየቱንም ገልጸዋል።
በመሆኑም ኢትዮጵያን ለማፍረስ እየሰራ ያለውን አሸባሪውን ህወሓት እየቆፈረ ባለው ጉድጓድ ለመቅበር በሚደረገው ጥረት ሁሉም የክልሉ ሕዝብ ከሀገር መከላከያ ሠራዊት ጎን በመሰለፍ መስዋትነት ለመክፈል እንዲዘጋጅ አሳስበዋል።
የክልሉ ሕዝብ አሸባሪው ህወሓት ሀገር ለማፍረስ ደቀነውን የህይወትና ህልውና አደጋ ለመቀልበስ ለተደነገገው የአስቸኳይ ጊዜ ዓዋጅ ስኬታማነት እንዲተባበር ርዕሰ መስተዳድሩ ጥሪ አቅርበዋል።
በሰልፍ ላይ የመንግሥት ሰራተኞች፣ ተማሪዎች፣ሴቶችና የጋምቤላ ከተማ ነዋሪዎች ተሳትፈዋል።