ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ከ17 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን ወደ ግማሽ ፍጻሜ አልፏል

አዲስ አበባ ነሐሴ 14/2010 በታንዛኒኒያ እየተካሄደ በሚገኘው የምስራቅና መካከለኛው አፍሪካ (ሴካፋ) የማጣሪያ እግር ኳስ ውድድር የኢትዮጵያ ከ17 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን የደቡብ ሱዳን አቻውን 5 ለ 1 በሆነ ውጤት ማሸነፍ ችሏል። በ2011 ዓ.ም በታንዛኒያ በሚካሄደው የአፍሪካ ከ17 ዓመት በታች የእግር ኳስ ውድድር የሴካፋ ዞንን ወክሎ የሚሳተፈውን ቡድን ለመለየት ከነሐሴ 4 ቀን 2010 ዓ.ም ጀምሮ በታንዛኒያ የማጣሪያ ጨዋታ እየተካሄደ ይገኛል። የኢትዮጵያ ከ17 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን ትናንት በቻማዚ ስታዲየም ከደቡብ ሱዳን ጋር ባደረገው ጨዋታ በምንተስኖት እንድርያስና ወንድማገኝ ኃይሉ ሁለት ሁለት ጎሎችና በአማኑኤል ተረፈ አንድ ጎል ማሸነፍ ችሏል። በዚህም መሰረት በአሰልጣኝ ተመስገን ዳና የሚመራው ብሔራዊ ቡድን ሶስት ጨዋታዎችን በማሸነፍ ወደ ግማሽ ፍጻሜ ማለፉን አረጋግጧል። ምድብ አንድንም በዘጠኝ ነጥብና በዘጠኝ የግብ ክፍያ እየመራ ሲሆን ብሔራዊ ቡድኑ በ3 ጨዋታዎች 10 ጎሎችን ሲያስቆጥር  አንድ ጎል ብቻ አስተናግዷል። የምድቡ የመጨረሻ ጨዋታውን ከነገ በስቲያ ከኬንያ አቻው ጋር የሚያደርግ ሲሆን ጨዋታውን ካሸነፈ ምድቡን በመሪነት በማጠናቀቅ በምድብ ሁለት ከሩዋንዳ ወይም ከአዘጋጇ ታንዛንያ ጋር ይጫወታል። ትናንት በምድብ አንድ በተደረገ ሌላ ጨዋታ ኡጋንዳ የኬንያ አቻውን 3 ለ 1 በሆነ ውጤት በማሸነፍ በስድስት ነጥብ ሁለተኛ ደረጃ ላይ መቀመጥ ችሏል። በምድብ ሁለት የአፍሪካ ከ17 ዓመት በታች የእግር ኳስ ውድድር የሴካፋ ዞን ውድድር አስተናጋጅ የሆነችው ታንዛንያና ሩዋንዳ በተመሳሳይ ስድስት ነጥብ በግብ ክፍያ ተበላልጠው በቅደም ተከተል አንደኛና ሁለተኛ በመሆን ወደ ግማሽ ፍጻሜ አልፈዋል። የሴካፋ ከ17 ዓመት በታች የእግር ኳስ ማጣሪያ ውድድር እስከ ነሐሴ 20 ቀን 2010 ዓ.ም ይቆያል። የማጣሪያ ውድድሩ በሰባት ዞን ተከፋፍሎ የሚካሄድ ሲሆን አሸናፊ የሚሆኑት ሰባት ብሔራዊ ቡድኖች በአፍሪካ ከ17 ዓመት በታች የእግር ኳስ ውድድር ተሳታፊ ይሆናሉ።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም