ቀጥታ፡

የቀረጥ ነፃ እድል (አጎዋ) በመከልከል ኢትዮጵያ ላይ ጫና የማሳደሩ ጥረት ተገቢነት የለውም

ጥቅምት 26/2014 (ኢዜአ) አሜሪካ ለኢትዮጵያ የሰጠችውን የቀረጥ ነፃ እድል / አጎዋ/ በመከልከል ጫና ለማሳደር የምታደርገው ጥረት ተገቢነት የሌለው ነው ሲል የትግራይ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ /ትዴፓ/ ገለጸ።

ፓርቲው አሸባሪው ህወሓት በሕዝብ ላይ የሚያደርሰውን ግፍ፣ መከራ፣ ጭቆናና አፈና ለማስቀረት በጦር ሜዳ ጭምር ለመፋለም መዘጋጀቱንም አስታውቋል።

አልጀዚራ በቅርቡ የአሜሪካ መንግስት ኢትዮጵያ ላይ የጣለውን የኢኮኖሚ ማዕቀብ አስመልክቶ 'እርምጃው የኢትዮጵያዊያንን የኢኮኖሚ ችግር ከማባባስ ውጭ በአገሪቷ ያለውን ግጭት አይፈታም' ሲል በዘገባው አመልክቷል።

የኢኮኖሚ ማዕቀብና ከአጎዋ የማስወጣት የቅጣት እርምጃዎች አገሪቷ ያሉባትን የኢኮኖሚ ተግዳሮቶች ማባባስ እንጂ መፍትሄ እንደማይሆኑ ነው በትንታኔው ያሳየው።

የትዴፓ ፓርቲ ሊቀመንበር ዶክተር አረጋዊ በርሄ ለኢዜአ ሲገልጹም ምዕራባዊያን በኢትዮጵያ ሕዝብና መንግስት ላይ የተለያዩ ጫናዎችን በማሳደር ሉዓላዊነቷን ለመጋፋት የሚያደርጉት ጥረት አይሳካም ይላሉ።

የኢትዮጵያ መንግስት የሕዝብ ይሁንታ አግኝቶ በምርጫ የመጣ በመሆኑም ማንም አካል እንደፈለገው ጫና በማሳደር ሊመራው እንደማይችል ተናግረዋል።

ሕዝቡም እድገቱን በራሱ ማምጣት እንደሚችል ተገንዝቧል ብለዋል ዶክተር አረጋዊ።

በሕዝብ ይሁንታ መንግስት የመሰረተውን ፓርቲ ተላላኪ ለማድረግና ዴሞክራሲን ለማፈን የሚያደረገውን ጥረት ዓለምአቀፉ ማኅበረሰብም ሊያወግዘው ይገባል ነው ያሉት።

በተለያዩ አካላት ኢትዮጵያን ለማዳከም የሚደረገው ጫና ሕዝቡ በቁጭት እንዲነሳሳ፣ እዲቆም፣ ራሱን ችሎ ልማቱን እንዲያካሒድና ጠንካራ አገር እንዲገነባ እያስቻለው መሆኑንም ተናግረዋል።

እነዚህ አካላት አሸባሪው ህወሓት ለበርካታ ዓመታት የኢትዮጵያን ሕዝብ ለስቃይ፣ ለሞትና ለእንግልት ሲዳርግ ዝምታን መርጠው ሲደግፉት እንደነበረም ጠቁመዋል።

ይህ ደግሞ ኢትዮጵያ ላይ ጫና የሚፈጥሩ የውጭ ሃይሎች የራሳቸውን ጥቅም ከማስከበር ውጭ የሕዝብ ፍላጎትና የአገር ሉዓላዊነትን የማስከበር ፍላጎት እንደሌላቸው ያሳያል ነው ያሉት።

እነዚህ ለዓመታት በዲፕሎማሲ፣ በኢኮኖሚና በፖለቲካ መስኮች ከሽብርተኛው ቡድን ጋር የሰሩ አካላት የኢትዮጵያ ሕዝብ ላሳለፈው ሰቆቃና የሠብዓዊ መብት ረገጣ ደንታቢሶች መሆናቸውን ጠቅሰዋል።

አሁንም የቀረጥ ነፃ ዕድል /አጎዋ/ን ጨምሮ ሌሎች ጫናዎችን በማሳደር ሕዝቡን ዳግመኛ ወደ ባርነት ለመመለስ እየሰሩ በመሆኑ ሕዝቡ መተባበርና በንቃት መንቀሳቀስ አለበት ብለዋል።

አሸባሪው ህወሓት ኢትዮጵያና ሕዝቦቿን ክዶ መከላከያ ሠራዊቱን ከጀርባው በመውጋት ራሱ ያፀደቀውን ሕገ መንግስት የሻረ እንደሆነም ዶክተር አረጋዊ ተናግረዋል።

ቡድኑ የትግራይን ሕዝብም በማስፈራራትና በስልጣን ጊዜው በነበረው የአንድ ለአምስትና ሌሎች መዋቅሮች በመጠቀም አፈናና ጭቆና እያደረሰበት መሆኑን ጠቅሰዋል።

ዶክተር አረጋዊ የትግራይ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ አሸባሪውን ቡድን ለመመከት አባላቱን በማደራጀት ወደጦር ግንባር ለመሄድ ዝግጁ መሆኑንም ገልጸዋል።

የህወሓት የሽብር ቡድን አገሪቷን ባስተዳደረባቸው ዓመታት ያደረሰውን ተደራራቢ ስቃይና መከራ የችግሩ ገፈት ቀማሽ የነበረው ሕዝብ ጠንቅቆ የሚያቀው ነው ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም