የክተት ጥሪውን በጠንካራ አደረጃጀት በመምራት አሸባሪው ህወሓትን ለመደምሰስ እየተሰራ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የክተት ጥሪውን በጠንካራ አደረጃጀት በመምራት አሸባሪው ህወሓትን ለመደምሰስ እየተሰራ ነው
ጥቅምት 26 ቀን 2014 (ኢዜአ) የአማራ ክልል ያስተላለፈውን የክተት ጥሪ ተቀብሎ ወደ ግንባር የሚዘምተውን ሃይል በጠንካራ አደረጃጀት በመምራት አሸባሪውን ህወሓት ለመደምሰስ በቁርጠኝነት እየተሰራ መሆኑን የብልጽግና ፓርቲ የአማራ ጽህፈት ቤት አስታወቀ።
የጽህፈት ቤቱ ሃላፊ አቶ ግርማ የሺጥላ ለኢዜአ ጋር እንዳሉት፤ አሸባሪውን ህወሓት ለመደምሰስ አስፈላጊውን መስዋዕትነት ለመክፈል ቁርጠኛ አቋም ተይዟል።
የአሸባሪውን የጥፋት ተግባር በተደራጀ አግባብ ለማስቆም አመራሩ በግንባር ህዝቡን በመምራት ጠላትን በመደምሰስ የአገር አንድነትን ለማስጠበቅ መተማመን ላይ መድረሱን ገልጸዋል።
የክተት ጥሪውን በጠራ አደረጃጀት በመምራት፣ የአካልና ወታደራዊ ስልጠና እንዲሁም የስነ ልቦና ግንባታ ስራ በማከናወን ለዘመቻው ውጤታማነት እንደሚሰራ አመልክተዋል።
የክልሉ መንግስት ባስተላለፈው የክተት ጥሪ ወደግንባር የሚዘምተው ሃይልም በራሱና በመንግስት ትጥቅ እንዲሟላለት መደረጉን አመልክተዋል።
አሸባሪው ህወሓት በስልጣን ላይ በቆየባቸው ዓመታት ኢትዮጵያን በጎሳ፣ በቋንቋ፣ በባህል፣ በሃይማኖትና በሌሎች መንገዶች በመከፋፈል እኩይ ሴራውን ሲፈጽም መቆየቱን ያስታወሱት አቶ ግርማ፤ ከዚህ ቡድን ጋር የሚካሄድ ጦርነት በተሟላ ዝግጅት በአጭር ጊዜ መጠናቀቅ እንዳለበት ገልጸዋል።
ህዝቡ ከውጭ ሃይሎች ጋር በማበር የመጣን ወራሪ ድል አድርጎ ለመመለስ የሚያስችል የዳበረ ልምድ እንዳለው ጠቁሜጨመዋል።
የቀረበውን የክተት ጥሪ በሙሉ ልብና ቁርጠኝነት የተቀበለው ህዝብ ወደ ግንባር እየተመመ መሆኑን ጠቅሰው፤ የህዝቡ እንቅስቃሴ አሸባሪውን በአጭር ጊዜ ውስጥ በመደምሰስ የሀገሪቱን ታሪክና ክብር አስጠብቆ የሚያስቀጥል መሆኑን ገልጸዋል።
"ጠላት በጦር ግንባር ብቻ ሳይሆን እብድ፣ የሃይማኖት አባትና ለማኝ በመምሰልና የተለያዩ ስልቶችን በመጠቀም በውስጣችን ለጥፋት እየተንቀሳቀሰ መሆኑን እናውቃለን" ብለዋል።
በተለያየ የባንክ ሂሳብ ቁጥር ገንዘብ የሚያንቀሳቅሱበት ደብተር፣ የጦር መሳሪያና መገናኛ በመያዝ ለአሸባሪ ቡድኑ መረጃ የሚያቀብሉ መኖራቸውንም ጠቁመዋል።
አሸባሪው ቡድንና ተላላኪዎቹ እያደረሱ ባለው ግፍ ከክልሉ ህዝብ ባለፈ በኢትዮጵያዊያን ላይ ከፍተኛ ቁጣና ብስጭት መቀስቀሱን ተናግረዋል።
የሽብርተኛው ህወሃት ተላላኪዎች በቡድኑ እኩይ ሴራ ከመጠለፍ አብረው ከኖሩት የኢትዮጵያ ህዝብ ጋር በመሰለፍ ለማይቀረው ድል የራሳቸውን አስተዋጽኦ እንዲያደርጉም ጥሪ አቅርበዋል።
በደጀንነት የሚያገለግለው ህዝብ ስንቅና ትጥቅ ከማቅረብ ባሻገር አካባቢውን ከባንዳዎችና ከሀዲዎች ነቅቶ እንዲጠብቅም አስገንዝበዋል።
_ አካባቢህን ጠብቅ፣
_ ወደ ግንባር ዝመት፣
_ መከላከያን ደግፍ።