ቀጥታ፡

የጥናት ሪፖርቱ የኢትዮጵያን ሃቅ በግልጽ ያሳየና የህወሓትን ከባድ ወንጀል ያጋለጠ ነው

ሐዋሳ፤ ጥቅምት 26/2014 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽንና የተባበሩት መንግስታት የሰብዓዊ መብት ቢሮ የጥናት ሪፖርት የኢትዮጵያን ሃቅ በግልጽ ያሳየና የአሸባሪውን ህወሓት ከባድ ወንጀል ያጋለጠ መሆኑን የሐዋሳ ዩኒቨርስቲ ምሁሯን አስታወቁ።

በዩኒቨርሲቲው የፖለቲካል ሳይንስና ዓለም አቀፍ ጥናት መምህርና ተመራማሪ ረዳት ፕሮፌሰር አወል ዓሊ ለኢዜአ እንደገለጹት አሸባሪው ህወሓት አሳፋሪ የሆኑ የሰብአዊ መብት ጥሰት ወንጀሎችን መፈጸሙን ይፋ የሆነው የጥናት ሪፖርት አረጋግጧል።

በተጨማሪም የኢትዮጵያ መንግሥት በዜጎች ላይ የሰብአዊ መብት ጥሰት አለመፈጸሙን ለዓለም ማህበረሰብ ማሳየቱን ተናግረዋል።

እውነታው ይህ ሆኖ ሳለ የአሸባሪውን ጥፋትና የሽብር ተግባር በማጋለጥ  ከእውነታ ጎን መቆም የነበረባቸው አንዳንድ ድርጅቶችና አገራት ወንጀሉን በመደበቅና የሀሰት ፕሮፖጋንዳውን በማስተጋባት ለአሸባሪው ህወሓት ያላቸውን ወገንተኝነት በግልጽ ማሳየታቸው  የሚያሳፍር መሆኑን አመልክተዋል።

ሪፖርቱ የተባበሩት መንግስታት የሰበዓዊ መብት ቢሮ  የኢትዮጵያን መንግስት በጅምላ ሲፈርጅ ከነበረበት አቋም ወጥቶ ሀቁን መቀበል መጀመሩን ያሳየ ነው፡፡

ሪፖርቱ የኢትዮጵያን ነባራዊ ሀቅ በዚህ ልክ አምኖ ማቅረብ መቻሉ መንግስትና ዜጎች ያደረጉት ርብርብ ውጤት መሳየት መጀመሩን አስረድተዋል።

ህወሓት የፈጸመው ከባድ ወንጀል ይበልጥ እስኪጋለጥና የኢትዮጵያ ዕውነታ በዓለም አደባባይ ገሃድ እስኪወጣ ድረስ ህብረተሰቡ የሚያደርገውን ትግል መቀጠል እንዳለበት አመላክተዋል።

አሸባሪው ህወሓት ኢትዮጵያን የማፍረስ የረዥም ዘመን ህልሙ በፈለገው ልክ አልሳካ ሲለው ክልሎችን በወረራ በመያዝ በዜጎች ህይወትና ንብረት ላይ ከፍተኛ እልቂት እያስከተለ እንደሚገኝ የገለጹት ምሁሩ  የአሸባሪውን ድርጊት የዓለም አቀፍ ማህበረሰብ ሊያስቆም እንደሚገባም አመልክተዋል።

ከተፈጠረበት ጊዜ ጀምሮ ከሴራና ወንጀል ውጭ አሻጋሪ ሀሳብ የሌለው አሸባሪው ህወሓት እቆመለታለሁ የሚለውን የትግራይን ህዝብ ለስቃይና እንግልት መዳረጉን ጠቁመዋል።

''አገር ለመበተን የተነሳውን ህወሓት ማንም ቆሞ አይመለከትም'' ያሉት ረዳት ፕሮፌሰር አወል ዜጎች "አዲሲቷን ኢትዮጵያ በህወሓት መቃብር ላይ እንድትለመልም ለማድረግ መዝመትና በምንችለው ሁሉ መታገል አለብን '' ብለዋል።

ጦርነቱ በህወሓት ቀስቃሽነት መጀመሩንና ይህን ተከትሎ ከፍተኛ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች መፈጸማቸውን አጥኚዎቹ በግልጽ ሪፖርት ማድረጋቸው በቂ አለመሆኑን የገለጹት ደግሞ በሐዋሳ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካል ሳይንስ ምሁሩ ዶክተር ንጉስ በላይ ናቸው ።

የጥናቱ ሪፖርቱ ለጦርነቱና ለተፈጸሙ ወንጀሎች መነሻና ምክንያት አሸባሪው ቡድን መሆኑን ማሳየቱን የጠቆሙት ምሁሩ ሪፖርቱ ወንጀል የተፈጸመባቸውን ሁሉንም ቦታዎች አለመዳሰሱ በእጥረት የሚታይ መሆኑን ተናግረዋል።

ሪፖርቱ የአሸባሪውን  ህወሓት የሀሰት ፕሮፖጋንዳ የሚዘውሩ አካላት ውንጀላን ውድቅ በማድረግ ቅጥፈታቸው በዓለም አደባባይ እንዲጋለጥ ማድረጉን ጠቁመዋል።

በጥናቱ ጥልቀትና ገለልተኝነት ላይ ጥያቄዎች እንዳሉ በመገንዘብ መንግስትና ዜጎች የኢትዮጵያ እውነት በግልጽ እስኪረጋገጥ የጀመሩትን ትግል ማጠናከር እንዳለባቸው ጠቁመዋል።

''ጥናቱ ትግራይ ላይ ብቻ ትኩረት ያደረገ ነው'' ያሉት ዶክተር ንጉስ፤ በሰሜኑ ክፍል በሚገኙ አፋርና አማራ ክልሎች በንጹሃን ዜጎች ላይ የተፈጸመው ወንጀሎች ሊተኮሩ እንደሚገባም አመልክተዋል ።

ለጥናቱ የተመረጡ ቦታዎች ተገቢነት ላይ ጥርጣሬ እንዳላቸው ያነሱት ዶክተር ንጉስ፤ በጥናቱ ሪፖርት ላይ በዓለም አቀፍ የጦርነት ህግ በተከለከሉ የሃይማኖት ተቋማትና ሌሎች ላይ  የተፈጸሙ ወንጀሎችን  በግልጽ ባለማሳየቱ የአሸባሪው ህወሓትን ሴራና ተንኮል በማጋለጥ ክፍተት ያለበት መሆኑን ጠቁመዋል።

በሪፖርቱ ሳንዘናጋ የአሸባሪውን ህወሓት አስከፊ ድርጊት ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ግልጽ ለማድረግ በመንግስትና በዜጎች የተጀመረው ርብርብ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽንና የተባበሩት መንግስታት የሰብዓዊ መብት ቢሮ በትግራይ ክልል ተፈጸሙ የተባሉ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን በሚመለከት ሲያከናውን የቆየውን የጥናት ሪፖርት ከትላንት በስቲያ ይፋ ማድረጉ ይታወቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም