በአገር ሕልውና እና ሉዓላዊነት ላይ የተደቀነውን አደጋ ለመከላከል የበኩላችንን እንወጣለን - ኢዜአ አማርኛ
በአገር ሕልውና እና ሉዓላዊነት ላይ የተደቀነውን አደጋ ለመከላከል የበኩላችንን እንወጣለን
አዲስ አበባ ጥቅምት 26/2014(ኢዜአ) የአገር ሕልውናና ሉዓላዊነት ላይ የተደቀነውን አደጋ ለመከላከል ተግባራዊ የሆነው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ተፈጻሚነት የበኩላቸውን እንደሚወጡ የሕዝብ ምክር ቤት አባላት ገለጹ።
መላው ሕዝብ ለአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ተፈጻሚነት ሃላፊነቱን እንዲወጣም ጥሪ አቅርበዋል።
የምክር ቤቱ አባል አምባሳደር ዲና ሙፍቲ በኢትዮጵያ ላይ የተከፈቱ የወታደራዊ፣ የምጣኔ ሃብትና የፕሮፓጋንዳ ጦርነቶች የአገር ሕልውናን እንደሚፈታተኑ ገልጸዋል።
እነዚህ ሃይሎች ከሌሎች የኢትዮጵያ ጠላቶች ጋር ተሻርከው በውግንና እየሰሩ ያለውን ተግባር ለመቀልበስ የጸደቀው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ያለውን ፋይዳም ገልጸዋል።
ምክር ቤቱም የሕዝብ ተጠሪ እንደመሆኑ የጸደቀውን አዋጅ ተግባራዊ በማድረግ ሂደት የአባላቱ ሚና ግንባር ቀደም እንደሚሆን ገልጸው እንደ ምክር ቤት አባልና እንደ ዜጋም የበኩላቸውን እንደሚወጡ ተናግረዋል።
የምክር ቤት አባሉ አቶ ክርስቲያን ታደለም የተለያዩ አካላት የተለያዩ አስተያየቶችን ቢሰጡም በኢትዮጵያ ጉዳይ ከዜጎቿ በላይ ወሳኝ ሊሆኑ እንደማይችሉ ተናግረዋል።
የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አፈጻጸም መርማሪ ቦርድ አባል የሆኑት አቶ ክርስቲያን ቀደም ሲል በነበሩ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጆች የመርማሪ ቦርድ አባል ስብጥር የፓርቲ ማዕከላዊነት ይንጸባረቅ እንደነበረ አስታውሰዋል።
የተሰጣቸውን ሃላፊነት በነጻነት በመከወን ለአዋጁ ተፈጻሚነት የበኩላቸውን እንደሚወጡም አረጋግጠዋል።
የምክር ቤቱ አባላት ኢትዮጵያዊያን በአገራቸው አንድነትና ሕልውና ላይ አደጋ የደቀነውን የሽብር ቡድን ለመደምሰስ እያደረጉ ያለውን ተጋድሎ እንዲያጠናክሩም ጠይቀዋል።
የውስጥ አንድነትን በማጠናከር የውጭ ጫናዎችን መቋቋም እንደሚቻልም አመልክተዋል።
የሽብርተኛው ህወሓት ቡድንና ግብር አበሮቹን እኩይ ዓላማ ለማሳካት በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች በንጹሃን ዜጎች ላይ የሚፈፀመው ግድያ፣ ዝርፊያና ሌሎች ኢ-ሠብአዊ ጥቃቶች እጅግ አደገኛ ደረጃ ላይ በመድረሳቸው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መታወጁ ይታወቃል።