የጥናት ሪፖርቱ የሕወሓትን አረሜኔያዊ ድርጊትና የሀሰት ትርክት በጋህድ ያጋለጠ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የጥናት ሪፖርቱ የሕወሓትን አረሜኔያዊ ድርጊትና የሀሰት ትርክት በጋህድ ያጋለጠ ነው
ሀዋሳ፤ ጥቅምት 25/2014 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽንና የተመድ ሰብዓዊ መብት ቢሮ ይፋ ያደረጉት የጥናት ሪፖርት የአሸባሪው ህወሓትን አረመኔያዊ ድርጊትና የሀሰት ትርክት በገህድ ያጋለጠ ነው ሲሉ የሀዋሳ ከተማ ነዋሪዎች ገለጹ።
የሀዋሳ ከተማ ነዋሪ መምህር መልካሙ ጉካሞ ለኢዜአ እንደገለጹት የጥናት ሪፖርቱ አሸባሪው ህወሓት የኢትዮጵያን መንግስት ሲከስ የነበረባቸውን የሀሰት ውንጀላዎች በዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ፊት ውድቅ ያደረገ ነው።
በሀሰት ትርክት ላይ የተመሰረተው አሸባሪው ህወሓት ራሱ በፈፀመው ጥፋት ሌላ አካልን ተጠያቂ ማድረግ እንደማይችል ያሳየ መሆኑን ጠቅሰዋል።
አቶ ስምዖን ከተማ በበኩላቸው አሸባሪው ህወሓት በንፁሀን ላይ ጭፍጨፋ ሲያካሂድ ትክክል የሚሆንበት ፤የኢትዮጵያ መንግስት ሕግ -የማስከበር እርምጃ ሲወስድ ደግሞ በተቃራኒው የንፁሀን ጭፍጨፋ ተካሄደ ብሎ የሚከስ ሀሰተኛ ቡድን እንደሆነ ተናግረዋል።
ይፋ የተደረገው የጥናት ሪፖርት ህወሀት የመከላከያ ሰራዊት ሰሜን እዝ አባላት ላይ ጥቃት በመፈጸም ጦርነት የጀመረበትንና በንጹዋን ዜጎች ላይ ጅምላ ጭፍጨፋ ማካሄዱን በገሀድ የወጣ መሆኑን ለአብነት ጠቅሰዋል።
ህወሀት በማይካድራና በጋሊኮማ በንፁሀን ላይ የፈፀመውን የጅምላ ጭፍጨፋ በማካድ በሌላ አካል ላይ ለማላከክ የሄደበትን ርቀትን አንስተዋል።
የጥናት ውጤቱ የኢትዮጵያ እውነት በዓለም አቀፍ ማህበረሰብ ዘንድ ተቀባይነት እንዲያገኝ የሚያስችል መሆኑን ተናግረዋል።
እውነቱ ከዚህም በበለጠ ግልፅ እንዲሆን ተጨማሪ ጥናቶች እንደሚያስፈልጉ ጠቁመዋል።
''የአሸባሪው ህወሓት የሀሰት ትርክት በሥልጣን ላይ በነበረበት ወቅት ስላየነው ውሸቱ ሊያስገርመን አይገባም'' ያለው ደግሞ ወጣት አብዱልረዛቅ ሸምሱ ነው።
ሪፖርቱ የአሸባሪውን ህወሓት አደገኛነት ፍንትው አድርጎ ያሳየ መሆኑን የገለጸው ወጣት አብዱልረዛቅ አገርን ከመፍረስ ለመታደግና ሰላም ለማረጋገጥ በተባበረ ክንድ ግብዓተ መሬቱን ማፋጠን እንደሚገባ ጠቁሟል።
አሸባሪው ህወሓት አሁን ላይ በተለያዩ የመገናኛ ብዙሃን አማራጮች የሚያሰራጫቸው ከእውነት የራቁ መረጃዎችን ወደ ጎን በመተው ሀገር በማዳን ዘመቻው ላይ ሁሉም አካል ሊረባረብ እንደሚገባ አመላክቷል።
የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽንና የተባበሩት መንግስታት የሰበዓዊ መብት ቢሮ በትግራይ ክልል ተፈጸሙ የተባሉ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን በሚመለከት ሲያከናውን የቆየውን የምርመራ ሪፖርት ከትናንት በስቲያ ይፋ ማድረጉ ይታወቃል።