ቀጥታ፡

የኢኮኖሚ ማእቀቡ መፍትሄ ከማምጣት ይልቅ ግጭቱን ያባብሰዋል

ጥቅምት 26 ቀን 2014 (ኢዜአ) አሜሪካ ኢትዮጵያ ላይ የጣለችው የኤኮኖሚ ማእቀብ መፍትሄ ከማምጣት ይልቅ ግጭቱን እንደሚያባብሰው በአሜሪካ ኦሬገን ስቴት ዩኒቨርሲቲ የኤኮኖሚክስ ፕሮፌሰር የሆኑት ካሳሁን ይልማ ገለጹ።

ድርጊቱ በሁለቱ አገራት መካከል ለረጅም ዘመናት ሲገነባ የቆየውን ግንኙነት ይጎደዋል ሲሉም አስጠንቅቀዋል።

ፕሮፌሰሩ ለአልጀዚራ በላኩት መጣጥፍ እንዳስቀመጡት የጆ ባይደን አስተዳደር ከ20 አመታት በፊት ከቀረጥና ከኮታ በሆነ ስርአት የአፍሪካ ምርቶች በአሜሪካ ገበያ እንዲያገኙ ከተመቻቸው እድል /AGOA/ ኢትይጵያን ማገዳቸውን ገልጸዋል።

በዚህም በምስራቅ አፍሪካ አንጻራዊ መረጋጋት ለነበራትና በህዝብ ቁጥሯ ከአፍሪካ በሁለተኛ ደሬጃ የምትቀመጠውና ለአሜሪካ የቀይባህር ስትራቴጂያዊ አጋር ለሆነችው ኢትዮጵያ ጥቅሙ ትልቅ ነበር ያሉት ፕሮፌሰሩ፤ ከግጭቱ በፊት ኢትዮጵያ በጸረሽብር ትግሉና በሰላም ማስከበሩ በኩልም ሚናዋ ከፍተኛ እንደነበር አስታውሰዋል።

ፕሮፌሰሩ የአሜሪካ ባለስልጣናት ደጋግመው እንደተናገሩት አሜሪካ ኢትዮጵያን ከመርሃግብሩ የምታስወጣት ከሆነ በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ የምርት ተግባር ላይ የተሰማሩ በርካታ ንጹሃን ተጎጂ እንደሚሆኑ ገልጸው ውሳኔው የኮቪድ-19 ወረርሽኝና ስራ አጥነት ባደቀቀው ምጣኔ ሃብት ላይ ሲደመር ጉዳቱን ያይለዋል ብለዋል።

ውሳኔው “የኢትዮጵያ መንግስትን የማስፈጸም አቅም በመጉዳት ለዜጎቹ መሰረታዊ ግልጋሎቶችን እንዳያቀርብ ሊያደርገው ይችላል” ሲሉም አብራርትዋል ፕሮፌሰር ካሳሁን ይልማ።

የ27ቱ አመት የህወሃት አገዛዝ ጠንካራ ተቃዋሚ እንዳይኖር በማድረጉ አሁን ላይ አማራጭ ሃሳቦችን እንደሚፈለገው ማግኘት አለመቻሉን ያስረዱት ፕሮፌሰሩ በህዝቦች ደም አፋሳሽ ትግል የተወገደውን ቡድን ድጋሚ ወደ ስልጣን ለመመለስ የሚደረገው ሙከራ ኢትዮጵያን ከማፈራረስና ለአስተዳደር የማይመች ቀጠና ከመፍጠር የዘለለ ውጤት አያመጣም ብለዋል።

አሁን ያለው መንግስት ባደረጋቸው ሪፎርሞች የተነሳ ታላላቅ ድርጅቶች የኢትዮጵያን ኩባንያዎች እየገዙና ስራቸውን ለማስፋፋት እየጣሩ ባለበት ወቅት ተጨማሪ እገዛዎች ሊደረጉለት ሲገባ ማእቀቦችን ለመጣል የሚደረገው ጥረት አደገኛ ብቻም ሳይሆን ውጤት አልባ መሆኑን ጠቅሰዋል።

ይህ የአሜሪካ ውሳኔ ለረጅም ዘመናት የቆየውን የሁለቱን አገራት ግንኙነት እንደሚጎዳው አስጠንቅቀዋል።

ፕሮፌሰር ካሳሁን አክለውም ማእቀቡ ለአጭር ጊዜ መፍትሄ ሊመስል ቢችልም ዘላቂ ችግር ይዞ እንደሚመጣ የአሜሪካ ፖሊሲ አውጭዎች ሊገነዘቡት ይገባል ሲሉ አሳስበዋል።  

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም