የሕልውና ዘመቻውን የሚደግፍና የአሜሪካን ጣልቃ ገብነት የሚቃወም ሠላማዊ ሰልፍ በዋሽንግተን ዲሲ ይካሄዳል - ኢዜአ አማርኛ
የሕልውና ዘመቻውን የሚደግፍና የአሜሪካን ጣልቃ ገብነት የሚቃወም ሠላማዊ ሰልፍ በዋሽንግተን ዲሲ ይካሄዳል
ጥቅምት 25/2014 (ኢዜአ) የሕልውና ዘመቻውን የሚደግፍና የአሜሪካን ጣልቃ ገብነት የሚቃወም ሠላማዊ ሰልፍ ጥቅምት 29 ቀን 2014 ዓ.ም በዋሽንግተን ዲሲ እንደሚካሄድ ተገለጸ።
ሠላማዊ ሠልፉ "በአገር ሕልውናና አንድነት አንደራደርም" በሚል መሪ ሀሳብ እንደሚካሔድ ተገልጿል።
የሠላምና አንድነት ለኢትዮጵያ ግብረ ሃይል በዲሲ አስተባባሪ አቶ ጣሰው መላከሕይወት፤ ሠላማዊ ሰልፉ በዋይት ሐውስ ፊት ለፊት በኢትዮጵያ ሠዓት አቆጣጠር ከቀኑ 10 ሠዓት ጀምሮ እንደሚካሄድ ለኢዜአ ገልጸዋል።
በሠልፉ ላይ ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም የህወሓት አሸባሪ ቡድን በፈጸመው ጥቃት በግፍ የተጨፈጨፉ የአገር መከላከያ ሠራዊት የሰሜን ዕዝ አባላትን በማስታወስ እንደሚዘከሩ ተናግረዋል።
ሠልፈኞቹ የአገርን ሕልውና ለማስጠበቅ መስዋዕትነት በመክፈል ላይ የሚገኙ የመከላከያ ሠራዊት አባላትና ሌሎችም የጸጥታ አካላት አጋርነታቸውንና ድጋፋቸውን ይገልጻሉ።
የህወሓት የሽብር ቡድን በአፋርና በአማራ ክልሎች በፈጸመው ወረራ በንጹሃን ላይ ያደረሰውን ጭፍጨፋ እንደሚያወግዙም አቶ ጣሰው ገልጸዋል።
የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን ኢትዮጵያን ከቀረጥ ነጻ ንግድ ተጠቃሚነት እድል /አጎዋ/ ያስወጡበትን ውሳኔ ሠልፈኞቹ እንደሚቃወሙም ነው ያስረዱት።
ፕሬዚዳንቱ ያሳለፉት ውሳኔ ተገቢ አለመሆኑንና እርምጃቸውን ቀልብሰው ኢትዮጵያን ወደ አጎዋ እንዲመልሱም ጥሪ ይቀርባል ብለዋል።
ሠላማዊ ሰልፈኞቹ ማዕቀብን ጨምሮ አሜሪካ በኢትዮጵያ ላይ የምትወስዳቸውን እርምጃዎች እንደሚያወግዙ ነው የተናገሩት።
አሜሪካ በኢትዮጵያ ላይ እያደረገች ያለችውን ያልተገባ ጫና እና ጣልቃ ገብነት የሚቃወሙ እንዲሁም የውጭ ጉዳይ ፖሊሲዋን ዳግም እንድታጤን የሚያሳስቡ መልዕክቶችም ይተላለፋሉ ብለዋል።
በተጨማሪም አሜሪካ በኢትዮጵያ ላይ የምታደርገውን ጫና እንድታቆም የሚያሳስብ ደብዳቤ ለዋይት ሐውስ ይሰጣል ነው ያሉት አቶ ጣሰው።
በሌላ በኩል በቅርቡ የቨርጂኒያ ግዛት ገዢን ለመምረጥ በተካሄደው ምርጫ ትውልደ ኢትዮጵያዊያን የነበራቸውን ሚና ለዴሞክራቲክ ፓርቲ እናሳውቃለን ብለዋል።
በምርጫው የሪፐብሊካን ፓርቲ ዕጩው ግሌን ያንግኪን የዴሞክራቲክ ፓርቲ እጩን ቴሪ ማካውሊፍን አሸንፈው የቨርጂኒያ ግዛት ገዢ ሆነው ተመርጠዋል።
በምርጫው ትውልደ ኢትዮጵያዊያን ለሪፐብሊካኑ ዕጩ ድምጽ መስጠታቸውንና ይሄን ያደረጉበት ምክንያትም በስልጣን ላይ ያለው ዴሞክራቲክ ፓርቲ በአሜሪካ እየተከተለ ያለውን የተሳሰተ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ እንዲያጤነው ለማሳሰብ እንደሆነም ነው አቶ ጣሰው ያስረዱት።
ትውልደ ኢትዮጵያዊያኑ በቀጣይ በአሜሪካ ግዛቶች በሚካሄዱ የአካባቢ ምርጫዎች የሪፐብሊካን ዕጩዎችን በመምረጥ ድምጻቸውን እንደሚያሰሙ ተናግረዋል።
በሠላማዊ ሰልፉ ላይ በአሜሪካ የተለያዩ ግዛቶችና ከተሞችን ጨምሮ በካናዳ ግዛቶችና ከተሞች የሚኖሩ በርካታ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን ይሳተፋሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ አመልክተዋል።
በሰሜን አሜሪካ የሚኖሩ የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ማኅበረሰብ አባላት በኢትዮጵያ ላይ የሚደረገውን ጫና እና ጣልቃ ገብነት የመመከት እንዲሁም የኢትዮጵያን አቋምና መልካም ገጽታ የሚያንጸባርቁ ስራዎችን ለማከናወን የጀመሯቸውን ስራዎች በተጠናከረ መልኩ እንደሚቀጥሉ አክለዋል።
ጥቅምት 29 ቀን 2014 ዓ.ም በዋሽንግተን የሚካሄደውን ሠላማዊ ሠልፍ የሠላምና አንድነት ለኢትዮጵያ ግብረ ሃይል በዲሲ፣ ከአገር ወዳድ ኢትዮጵያዊያንና የተለያዩ ተቋማት በትብብር ያዘጋጁት መሆኑ ታውቋል።