ቀጥታ፡

በህልውና ዘመቻው በግንባር ቀደምነት እንሰለፋለን - የድሬዳዋ ነዋሪዎች

ድሬዳዋ ፤ ጥቅምት 25/2014 (ኢዜአ) ሀገርን ለማዳን በሚካሄደው የህልውና ዘመቻ በግንባር ቀደምነት ለመሰለፍ መነሳሳታቸውን የድሬዳዋ አስተዳደር ነዋሪዎች አስታወቁ።

 የከተማዋ ዘጠኝ ቀበሌ ነዋሪዎች   በወቅታዊ ሀገራዊ ጉዳዮች ዙሪያ  ዛሬ  ተወያይተዋል።

ነዋሪዎቹ በውይይት መድረኩ፤ ከሀገር መከላከያ ሠራዊት ጎን ለመሰለፍ የአሸባሪውን  ህወሃትና ጀሌዎቹን ከሰራዊቱ ጎን ተሰልፈው ለመዋጋት ዝግጁ መሆናቸውን ተናግረዋል።

በደጀንነትን ስንቅ ከማዘጋጀት ባሻገረ የአካባቢያቸውን ሰላም በማስጠበቅ ተሳትፎ እንደሚያደርጉ አስታውቀዋል።

ከውይይቱ ተሳተፊዎች መካከል  ወጣት ጀማል አልዩ፤ አሸባሪው  ህወሃትን ለመፋለም ወደ ግንባር በመዝመት ለሀገር ህልውና መስዋዕት ለመሆን ተዘጋጅቺያለሁ ብሏል።  

ሀገርን ለማፈራረስ የሚነዙትን አሉባልታዎችና ከፋፋይ ወሬዎች ባለመስማት እንደሚከላከልም ገልጿል።

በየቀበሌው ሠራዊቱን መቀላቀል ለሚፈልጉ ወጣቶች መመዝገቢያ ሥፍራዎች መዘጋጀት እንዳለባቸው ያማለከተው ደግሞ  ወጣት አንተነህ በላይ ነው።

ወጣት ሙስጠፋ መሐመድ በበኩሉ፤ አሸባሪው ህወሃት ትምህርት እንዲቋረጥ ፣ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ እንዲገታና ሰላምን በማናጋት እያደረገ ያለውን ጥረት ማክሸፍ አለብን ብሏል።

ነዋሪዎች በተለይ ወጣቶች የተደቀነብንን ሀገራዊ አደጋ ለመመከት በቁርጠኝነት መዝመትና የአባቶቻችን ታሪክ መድገም ይኖርብናል ሲልም አክሏል።

የቀድሞ ሠራዊት አባል  ሻለቃ ግርማ አበበ ፤ የኢትዮጵያ የመከላከያ ሠራዊት በየትኛውም ዘመን የሀገሪቱ ሉአላዊነትና ህልውና ለመድፈር የመጣን የውስጥና የውጭ ጠላት በመመከት  ታሪክ ማስመዝገቡን አስታውሰዋል።

አሁንም ከፍጥረቱ ለሀገር መፍረስ እየሰራ የሚገኘውን አሸባሪው የህወሃት ቡድን ለመገርሰስ በሚካሄደው እንቅስቃሴ ባላቸው ልምድ ወጣቱን ለማሰልጠን መዘጋጀታቸውን አስታውቀዋል።

ወይዘሮ አልማዝ ሰብስቤ" እኛ ሴቶች ተደራጅተን የአካባቢያችንን ሰላም እየጠበቅን ነው፤ካስፈለገ ግንባር በመዝመት የጦሩን ስንቅ በማዘጋጀትና ጥይት በማቀበል ሀገር ለማዳን ተዘጋጅተናል" ብለዋል።

ሀገርን ለማዳን አሁኑኑ በተቀናጀ መንገድ ተሰልፈን ወደ ግንባር ለመዝመት ዝግጁ ነኝ ያሉት ደግሞ ሼህ ዩሱፍ አብዱላሂ ናቸው።

ቡድኑ ሀገር ባስተዳደረባቸው ዘመናት የድሬዳዋን ሕዝብ የኑሮ መሠረት የሆኑትን ፋብሪካዎች በመዝረፍና የበርካታ  ቤተሰቦች መተዳደሪያ የነበረውን ምድር ባቡር በመበተን ጉዳት ማድረሱን በማስታወስ።

ወይዘሮ መልካም ተፈራ በበኩላቸው፤ በከተማዋ የአሸባሪው  ተላላኪዎችን መንጥሮ ለማውጣት ፍተሻ መካሄድ እንዳለበት ጠቁመዋል።

ከዚህ በተረፈ ለሠራዊቱ ስንቅ በማዘጋጀት ፣በጦርነት የተፈናቀሉትን በመደገፍ ፣ የዘማች ቤተሰቦችን በመርዳት ሀገራዊ ግዴታችንን እንወጣለን ብለዋል።

የድሬዳዋ አስተዳደር ከንቲባ ከድር ጁሃር ፤ሀገርን ለማዳንን የተጀመረው የህልውና ዘመቻ በፍጥነት እንዲጠናቀቅ በየትኛውም ረገድ ዋናው ሥራ ተደርጎ እየተከናወነ መሆኑን ገልጸዋል።

በነዋሪዎቹ ለተነሱት ጉዳዮች ላይ ትኩረት እንደሚሰጥም ከንቲባው አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም