ቀጥታ፡

የህወሓት የክህደት ወንጀል በታሪክ ጥቁር ጠባሳ የጣለ አረመኔያዊ ተግባር ነው - ነዋሪዎች

ጎንደር ጥቅምት 25/2014 (ኢዜአ) ''አሸባሪው ህወሓት በሀገር መከላከያ ሠራዊት ሰሜን እዝ አባላት ላይ ጥቃት በመፈጸም የፈጸመው የሀገር ክህደት ወንጀል በታሪክ የሚታወስ ጥቁር ጠባሳ የጣለ አረመኔያዊ ተግባር ነው'' ሲሉ የጎንደር ከተማ ነዋሪዎች ገለጹ፡፡
"አልረሳውም፣ እኔም የኢትዮጵያ ሠራዊት ነኝ'' በሚል መሪ ሃሳብ ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም በሸባሪው ህወሓት በግፍ የተሰዉ የሰሜን እዝ አባላት በጧፍ ማብራትና በህሊና ጸሎት ታስበዋል።

በጎንደር ከተማ መስቀል አደባባይ በሚገኘው አጼ ቴዎድሮስ መታሰቢያ ሃውልት በተካሄደ ስነስርአት ላይ ከታደሙት ነዋሪዎች መካከል አቶ ታሪኩ መኳንንት "እለቱ ታሪክ ሁሌም የማይረሳው ጥቁር ጠባሳ ጥሎ አልፏል" ብለዋል።  

ቀኑ መታሰቡ በአሸባሪው ህወሓት በተፈጸመ አረመኔያዊ ተግባር ለሀገራቸው ክብር ሲሉ የተሰው የመከላከያ ሠራዊት አባላትን ትውልዱ እንዲዘክራቸው የሚያደርግ መሆኑን ገልጸዋል።

አቶ ታሪኩ እንዳሉት የሽብር ቡድኑ ዛሬም ቢሆን የጥፋት ተግባሩን ቀጥሎበት በአማራ ህዝብ ላይ የሚያደርሰውን የከፋ ጭፍጨፋ አጠናክሮ ቀጥሏል።

"ጥቅምት 24ን ስናስብ የወራሪውን ህወሓት የጥፋት ተግባር ለማስቆምና ለመደምሰስ በእልህና በቁጭት በመነሳት ነው" ብለዋል፡፡

የሽብር ቡድኑ በሀገር መከላከያ ሠራዊት ላይ የፈጸመው አስነዋሪ የክህደትና የአረመኔ ተግባር ኢትዮጵያ በታሪኳ ተፈጽሞባት እንደማያውቅ የገለጸው ደግሞ ፋኖ አሸናፊ ዮሐንስ ነው፡፡

"በተለያዩ ጊዜያት ወደ ኢትዮጵያ የመጡ ወራሪዎችም ህዝብን ከህወሓት በላይ አላዋረዱም፤ ሀገራችንንም በዚህ ደረጃ አልደፈሯትም" ሲል የአሸባሪውን የሀገር ክህደት ገልጻል።

"እለቱ በየዓመቱ ሊዘከር ይገባል" ያለው ፋኖ አሸናፊ፣ በተለይ ወጣቱ ሀገር እንዳይፈርስ፣ ቤተሰቡ እንዳይገደል፣ ሚስቱንና እህቱ እንዳይደፈሩ የሽብር ቡድኑን አምርሮ መታገል እንዳለበት አሳስቧል።

እሱም ለነጻነቱና ለህልውናው ሲል አስፈላጊውን ሁሉ መስዋዕትነት ለመክፈል መዘጋጀቱን አረጋግጧል።

አቶ ያኸያ ያሲን የተባሉ ሌላው የከተማው ነዋሪ በበኩላቸው ሀገር ታፍራና ተከብራ የምትኖረው የውድ ልጆቿ ፍሬ በሆነው ሀገር መከላከያ ሠራዊት መሆኑን ተናግረዋል።

አምና ጥቅምት 24 በመከላከያ ሠራዊት የሰሜን አዝ ላይ የተፈጸመው የክህደት ወንጀልና ግፍ በኢትዮጵያ ታሪክ ያልታየ አሳፋሪ ተግባር መሆኑን ገልጸዋል፡፡

"እኔ ያልመራኋት ኢትዮጵያ አትኖርም፣ ሲኦልም ገብቼ ቢሆን አፈርሳታለሁ በሚል ሀግር ለመበተን ቆርጦ የተነሳው ህወሓት በሰሜን እዝና በንጹሀን ላይ የፈጸመው ጭፍጨፋ ሁሌም አረመኔ መሆኑን ማሳያ ነው" ብለዋል።

በድርጊቱ ኢትዮጵያዊያንን ከማሳዘን ባለፈ ቁጭት ውስጥ መክተቱን ያስታወሱት አቶ ያኸያ አሁን ላይ ህልውናን ከማቆየትና ሀገር ከማዳን በላይ ቅድሚያ የሚሰጠው ነገር ስለሌለ ለክተት ጥሪው መዘጋጀታቸውን ተናግረዋል።    

"ሰራዊት የሌለው ህዝብና ሀገር ህልውና የለውም፣ በመሆኑም ዛሬ ላይ የተደቀኑብንን ፈተናዎች ለመሻገር ሠራዊቱን ማገዝና ማበርታት ይገባል" ብለዋል።  

"ወጣቱ ብቻ ሳይሆን እኛ ሽማግሌዎችም ብንሆን በግንባር ከጠላት ጋር ተናንቀን ለህልውናችን ስንል መስዋዕትነት መክፈል አለብን" ሲሉም አቶ ያኸያ አክለዋል፡፡

የጎንደር ከተማ ነዋሪዎች ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓም በሰሜን እዝ አባላት ላይ የተፈጸመውን ግፍ ጧፍ በማብራትና በህሊና ጸሎት ያሰቡት ሲሆን ቀስቃሽና የሀራዊ ፍቅር የሚያንጸባርቁ የስነ ግጥምና ልዩ ልዩ የኪነ ጥበብ ዝግጅቶች ለታዳሚዎች ቀርበዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም