ቀጥታ፡

በሁለተኛው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ዘመን የ4ሺህ579 ኪሎ ሜትር መንገድ ደረጃ ማሻሻል፣ እድሳትና ግንባታ ተካሂዷል

አዲስ አበባ  ነሀሴ 13/2010  የኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን በሁለተኛው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ዘመን የ4 ሺህ 579 ኪሎ ሜትር መንገድ ደረጃ ማሻሻል፣ እድሳትና ግንባታ ማካሄዱን ገለጸ። ባለስልጣኑ የዕቅድ ዘመኑ የሶስት አመት አፈጻጸም ከፍተኛ እንደሆነም አመልክቷል። ሁሉን አቀፍ የገጠር መንገዶች ልማት ፕሮግራም አፈጻጸም እጅግ ዝቅተኛ መሆኑም ተጠቁሟል። የባለስልጣኑ የኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ሳምሶን ወንድሙ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ ከ2008 ዓ.ም እስከ 2010 ዓ.ም ባሉት ሶስት አመታት 5 ሺህ 779 ኪሎ ሜትር መንገድ ለማልማት በእቅድ ተይዞ ወደ ስራ ተገብቷል፡፡ በተለይም በመንገድ አውታር ያልተዳረሱ የአገሪቱን ክፍሎች ማዳረስና የጠጠር መንገዶችን ደረጃ ማሳደግ በዕቅድ ዘመኑ ትኩረት የተሰጠው እንደሆነ አመልክተዋል። በመሆኑም በዋና ዋና መንገዶች ማጠናከር፣ በአገናኝ መንገዶች ደረጃ ማሻሻልና ማሳደግ የፈጣን መንገዶች ግንባታ በሶስት አመት ውስጥ 4 ሺህ 579 ኪሎ ሜትር መስራቱን ጠቁመዋል። በተጨማሪም የከባድ ጥገና አንጻርም 2 ሺህ 803 ኪሎ ሜትር በእቅድ ተይዞ ከ4 ሺህ ኪሎ ሜትር በላይ መሰራቱን የኮሙኒኬሽን ዳይሬክተሩ ተናግረዋል፡፡ ያልተሰሩ ስራዎችም በተያዘው አመት ተካተው የአምስት አመቱ የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ እንዲሳካ የሚሰራ መሆኑን አቶ ሳምሶን አስታውቀዋል፡፡ በሌላ በኩል በክልሎች በኩል ተፈጻሚ የሚሆነው ሁሉን አቀፍ የገጠር መንገዶች ልማት ፕሮግራም እስከ 90 ሺህ ኪሎ ሜትር መንገድ ለመገንባት ታቅዶ ወደ ስራ ቢገባም አፈጻጸሙ ግን ከአስር በመቶ እንዳልበለጠ ነው የተገለጸው፡፡  በሁሉን አቀፍ የገጠር መንገድ ተደራሽነት ፕሮግራም መጓተት ዋነኛ ምክንያትም ለስራው በቂ ትኩረት አለመስጠት መሆኑን የተናገሩት ዳይሬክተሩ ችግሩን ለመፍታት ባለስልጣኑ ከክልል መስተዳድሮችና ጉዳዩ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ውይይት በማካሄድ የመፍትሔ አቅጣጫ ማስቀመጡን ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም