ቀጥታ፡

ለአገራቸው ክብርና አንድነት የሚታገሉ በግንባር ሲዘምቱ፤ ቀሪው ህዝብ ደግሞ አካባቢውን እንደ ሠራዊት ሆኖ መጠበቅ አለበት

አዲስ አበባ ጥቅምት 25/2013 /ኢዜአ/ ለአገራቸው ክብርና አንድነት የሚታገሉ በግንባር ሲዘምቱ፤ ቀሪው ህዝብ ደግሞ አካባቢውን እንደ ሠራዊት ሆኖ መጠበቅ እንዳለበት የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ አሳሰቡ።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ለመጀመሪያ ዙር የሕልውና ትግሉን የሚቀላቀሉ የመስተዳድሩ አመራሮችን  ሸኝቷል።

በዚሁ የሽኝት መርሃ-ግብር ላይ የከተማ አስተዳደሩ ከንቲባ አዳነች አቤቤን ጨምሮ ሌሎች ከፍተኛ ሥራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።

ከንቲባዋ በዚሁ ጊዜ ባስተላለፉት መልዕክት ዘማች አመራሮቹ ብቻ ሳይሆኑ ''ሁላችንም ዘማቾች ነን'' ብለዋል።

''ለኢትዮጵያዊነታችን፣ ለግዛትና ለውስጣዊ አንድነታችን ሁላችንም እንታገላለን'' ነው ያሉት።

ጥንት የኢትዮጵያ አባቶች መስዋዕትነት ከፍለው ነጻ አገር ለትውልድ እንዳስረከቡ አስታውሰው፤ የአሁኑ ትውልድ የራሱን ታሪክ የሚጽፍ እንጂ የተጻፈ ታሪክ የሚያበላሽ ባለመሆኑ የሀገሩን ክብር ለመጠበቅ ዝግጁ መሆኑን ገልጸዋል።

የተሸኙ ዘማቾች "ድል እንደሚያደርጉ ጥርጥር የለኝም" ሲሉም ነው የተናገሩት፡፡

ዘማቾቹ ለአገራቸው ክብር ሲዋደቁ ቀሪው ሕዝብ ደግሞ ልክ እንደ መከላከያ ሠራዊት ሆኖ አካባቢውን መጠበቅ እንዳለበትም አሳስበዋል።

ከዘማቾቹ መካከል አንዱ የሆኑት አቶ አቤል በቀለ ''ከሁሉም በላይ በተግባር ለአገር ዘብ ሆነህ ከመታየት በላይ የሚያስደስት ነገር የለም፤ ደስ ብሎኛል'' ብለዋል።

ነጻነት ያለ መስዋዕትነት እንደማይገኝ ገልጸው፤ ከዚህ አኳያ ኢትዮጵያውያን አሸባሪው ህወሓትን ለማጥፋት በአንድነት መነሳት እንዳለባቸው ጥሪ አቅርበዋል፡፡

በተለይ ወጣቶች አገራቸውን ለመታደግ እንዲነሱም ጠይቀዋል።

ሌላው ዘማች አመራር አቶ ጥሩዓለም ባሳዝነውም በበኩላቸው አረመኔውን የህወሓት ቡድን እስከመጨረሻው ከኢትዮጵያ ምድር ለማስወገድ ሁሉም በአንድነት የሚነሳበት ጊዜ አሁን መሆኑን ጠቅሰዋል።

ኢትዮጵያውያን ተባብረው አሸባሪውን የህወሓት ቡድን በማጥፋት ሀገራቸውን መታደግ እንዳለባቸውም ጠይቀዋል፡፡

ዛሬ የተሸኙት አመራሮች ለመጀመሪያ ዙር ሲሆን በሌሎች ዙሮች ደግሞ በርካታ የከተማዋ ነዋሪዎችና አመራሮች የሕልውና ትግሉን እንደሚቀላቀሉ ይጠበቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም