ቀጥታ፡

ማህበሩ በጎርፍ ለተፈናቀሉ አርብቶ አደሮች የቁሳቁስ ድጋፍ አደረገ

ጂንካ፤ ጥቅምት 25/2014 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር በደቡብ ኦሞ ዞን ዳሠነች ወረዳ በጎርፍ አደጋ ለተፈናቀሉ አርብቶ አደሮች ከ2 ነጥብ 5 ሚሊየን ብር በላይ ዋጋ ያላቸው ቁሳቁሶች ድጋፍ አደረገ።
ማህበሩ ድጋፉን ያደረገው በኦሞ ወንዝ ሙላት በደረሰ የጎርፍ አደጋ በወረዳው በቡቡኣና በኦቾሎች ቀበሌ ለተፈናቀሉ  700  አባወራና እማወራዎች ነው።

በማህበሩ የደቡብ ቅርጫፍ ኃላፊ አቶ ኢብራሂም ተማም እንዳሉት ድጋፉ የንፅህና መጠበቂያዎች፣ አልባሳትንና የቤት ውስጥ መገልገያ ቁሳቁሶችን ያካተተ ነው።

አደጋው ከተከሰተበት ዕለት ጀምሮ አንቡላንስ በመመደብ ተጎጂዎች የህክምና አገልግሎት እንዲያገኙ መደረጉን የገለጹት ደግሞ በማህበሩ የጂንካ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ጥላሁን ቢሻው ናቸው።

ማህበሩ በአገሪቱ በተለያዩ አካባቢዎች በሚፈጠሩ ሰው ሰራሽና ተፈጥሯዊ አደጋዎች ለተጎዱ ወገኖች ፈጥኖ በመድረስ ሰብዓዊ ድጋፍ እያደረገ መሆኑን ተናግረዋል።

ድጋፍ ከተደረገላቸው መካከል አርብቶ አደር ኤርጊች ናፓቶኮሪ በመስከረም 2014 ዓም  መጀመሪያ በኦሞ ወንዝ ሙላት በተከሰተ የጎርፍ መጥለቅለቅ በመኖሪያ ቤታቸውና ንብረታቸው  ላይ ጉዳት መድረሱን ተናግረዋል።

በጎርፉ ምክንያት ያፈሩት ሀብትና ንብረት መውደሙን የገለጹት አርብቶአደሩ ቀይ መስቀልን ጨምሮ የተለያዩ መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች እያደረጉላቸው ላለው ድጋፍ አመስግነዋል።

"አካባቢውን ያጥለቀለቀው ጎርፍ ባለመቀነሱ ወደ መኖሪያችን መመለስ አልቻልንም" ያሉት ደግሞ አርብቶ አደር ካላ አቹሌ ናቸው።

አሁን ላይ ለከብቶቻቸው የመኖ እጥረት ያጋጠማቸው በመሆኑ የሚመለከተው አካል ድጋፍ እንዲያደርግላቸው ጠይቀዋል ።

በደቡብ ኦሞ ዞን ዳሰነች ወረዳ ከመስከረም ወር 2014 ጀምሮ በተከሰተ የኦሞ ወንዝ ሙላት ከ36 ሺ በላይ  አርብቶ አደሮች መፈናቀላቸው ይታወሳል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም